Home / ፖለቲካ / የደብረሲና ከተማ ከንቲባ አቶ ወንድምሲገኝ ማሙዬ ተገደሉ

የደብረሲና ከተማ ከንቲባ አቶ ወንድምሲገኝ ማሙዬ ተገደሉ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በጣርማበር bወረዳ የምትገኘው የደብረሲና ከተማ ከንቲባ አቶ ወንድምሲገኝ ማሙዬ በትላንትናው ዕለት መገደላቸው ተረጋገጠ።

ከንቲባው ህይወታቸው ሊያልፍ የቻለው በታጣቂዎች በተተኮሰባቸው ጥይት መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል። ድርጊቱ የተፈጸመው ከንቲባው በከተማዋ ውስጥ በስራ እንቅስቃሴ ላይ በነበሩበት ወቅት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ስለ ጥቃቱ መንስኤም ሆነ ስለ አጥቂዎቹ ማንነት እስካሁን በይፋ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።

የደብረሲና ከተማ እና የጣርማበር ወረዳ አስተዳደሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የከንቲባውን ግድያ አረጋግጠዋል። አስተዳደሩ በሰጠው መግለጫ የግድያ ድርጊቱን “አሰቃቂ” ሲል የገለጸው ሲሆን፣ አቶ ወንድምሲገኝ ለከተማዋ እድገትና ለህዝብ አገልግሎት ሲተጉ የነበሩ መሪ መሆናቸውን ጠቅሷል።

በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ እና የግድያውን ፈጻሚዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴ ከመንግስት በኩል እስካሁን ተጨማሪ ማብራሪያ አልተሰጠም።

በክልሉ ባለው ጦርነት ምክንያት በርካታ ግድያዎች እና ድንገተኛ ጥቃቶች እየተለመዱ መምጣታቸው የታወቀ ሲሆን፤ ይህም ደግሞ በክልሉ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጥላ አጥልቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ክልሉን ወደ ፍጹም ሰላም የመመለስ ስራ እየተሰራ መሆኑን እና ይህም ውጤታማ መሆኑን በተለያዩ መድረኮች እያስታወቁ ይገኛሉ።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *