የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የአድማ ብተና እና የመደበኛ ፖሊስ አባላት በሙሉ የታጠቁትን የጦር መሣሪያ እስከ ነገ ጥር 7 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ገቢ እንዲያደርጉ አስቸኳይና ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጠ።
ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ውሳኔው የተላለፈው በክልሉ ካለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከክልሉ ኮማንድ ፖስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ነው ተብሏል። በዚህም መሠረት ከጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት በፊርማ ወጥተው በእጅ ላይ የሚገኙ ማንኛውንም የጦር መሣሪያዎች እስከ ነገ ጥር 7 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ድረስ ገቢ መደረግ እንደሚኖርባቸው ተገልጿል። ከተጠቀሰው የጊዜ ገደብ በኋላ የጦር መሣሪያ ይዞ የተገኘ ማንኛውም የፀጥታ አካል እንደ “ፀረ-ሰላም” ኃይል እንደሚቆጠር እና መንግሥት ለሚወስደው ማንኛውም ዓይነት እርምጃ ግለሰቡ ራሱ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቋል።
ይህ እርምጃ በክልሉ ያለውን የፀጥታ መዋቅር ይበልጥ ለመቆጣጠርና ሰላምን ለማስከበር የታለመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ሁሉም የፖሊስ አባላት መመሪያውን በአግባቡ እንዲተገብሩ ጥብቅ ማሳሰቢያ መሰጠቱ ተመላክቷል።












