በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ፣ በአካባቢው የወደፊት አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ከፍተኛ የሃሳብ ልዩነት መኖሩን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።
ለሪፖርተር ጋዜጣ የቀድሞውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ የሆኑትን አቶ ጌታቸው ረዳን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው፣ የፌደራል መንግስት በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል አወዛጋቢ በሆኑ አካባቢዎች ያሉ የአሁኑን መስተዳድሮች ለማፍረስ ዝግጅት እያደረገ ነው ብሏል ዘገባው።
አቶ ጌታቸው ለጋዜጣው በሰጡት ቃል፣ ይህ እርምጃ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ለማመቻቸትና የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል። አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው፣ እ.ኤ.አ በ2026 ተፈናቃዮች በፈቃደኝነትና በክብር የሚመለሱበት ሂደት መጀመር እንዳለበት መናገራቸውንና ለዚህም በኢትዮጵያውያን የሚመራና በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፍ ሂደት አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል።
አምባሳደሩ በሁመራ ቆይታቸው የወደሙ መሠረተ ልማቶችንና የሕክምና አገልግሎት እጥረቶችን መታዘባቸውን ገልጸው፣ አሜሪካ ከድንገተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ባለፈ ለዘላቂ ሰላም ከኢትዮጵያ ጋር አብራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውም በዘገባው ተካቷል።
ይሁን እንጂ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው ይህንን መረጃ ውድቅ በማድረግ ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ምላሽ ሰጥተዋል። ዋና አስተዳዳሪው አስተዳደሩ ሊፈርስ ነው የሚለው መረጃ መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይገናኝና የከሰረ የፖለቲካ ማደናገሪያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ዞኑ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል መዋቅር ስር በሙሉ የፌደራል መንግስት እውቅና እየተመራ መሆኑንና ይህም የሕዝቡን የቆየ የማንነት ጥያቄ የመለሰ ህጋዊ አሰራር መሆኑን አቶ አሸተ አብራርተዋል። ስለ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ጉብኝትም ሲያስረዱ፣ አምባሳደሩ ወደ አካባቢው የመጡት የዞኑ አስተዳደር ባቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ መሠረት የታሪክና የፍትሕ እውነታውን በአካል ለመረዳት እንጂ መዋቅር ለማፍረስ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በውይይቱም ወቅት የአካባቢው ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ወሰን ተከዜ ወንዝ መሆኑንና አካባቢውን “ምዕራብ ትግራይ” ብሎ መጥራት የታሪክ ስህተት መሆኑን ለልዑኩ ማስረዳታቸውን ጠቁመዋል። አቶ አሸተ አክለውም ሰላማዊ ተፈናቃዮች የመመለስ መብት ቢኖራቸውም፣ ይህም መሆን ያለበት የአካባቢውን የአማራ ማንነት በማክበርና በማይካድራ ግፍ የፈጸሙ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ በማድረግ መሆኑን አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በፌደራል መንግስት በኩል መዋቅሮችን ስለማፍረስ የወጣ ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ እና በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው መካከል ያለው ግልጽ የሃሳብ ልዩነት በአካባቢው የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ላይ የፖለቲካ ንትርኩ መቀጠሉን አመላካች እየሆነ መምጣቱ እየታየ ነው።












