የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ተገድለዋል
በጋምቤላ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት እና ብሔር ተኮር ሆኖ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፤ በመንግስት የጸጥታ ተቋማት ውስጥ ያሉ አንዳንድ አባላትም በግድያዎች ውስጥ እጃችው እንዳለባቸው እና የብሔር ግጭት መልክ እንዲይዝም ማድረጋቸው ተገልጿል።
ነዋሪዎች እና የክልሉ የጸጥታ ቢሮ ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ልዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል።
የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ በቅርቡ በተቀሰቀሰው ብሔር ተኮር ግጭት ወቅት፣ የፖሊስ አባላትም በግልጽ ወገንተኛ በመሆን ወደ አንድ ብሔር በማተኮር የግድያ ጥቃት እየፈጸሙ ነው። ይህ የፖሊስ አባላት ተሳትፎ የዜጎችን እምነት በጸጥታ አካላት ላይ እንዲሸረሸር ከማድረጉም በላይ የጥቃቱን መጠን እና ውስብስብነት ከፍ እንዲል አድርጎታል ብለዋል።
ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የጸጥታ ኃይሎች ገለልተኛ ሆነው ከመስራት ይልቅ በአካባቢው ያለውን ግጭት በማባባስ፣ ለጥቃቶች ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ ሲሉ ክስ አቅርበዋል።
የጋምቤላ ክልል ጸጥታ ቢሮ በሰጠው መግለጫ፣ በጸጥታ አካላት ውስጥ ያሉ አንዳንድ አባላት ወገንተኛ በመሆን ጥቃት የሚፈጽሙ መኖራቸውን አስታውቋል።
ይህ የክልሉ የጸጥታ አካል እውቅና መሰጠቱ የነዋሪዎችን ክስ የሚያጠናክር ሲሆን፣ በምዋቅር ውስጥ ያለውን የብሔር ክፍፍል እና የትዕዛዝ ሰንሰለት መላላት እንደሚያሳይም ተጠቁሟል።
ግጭቱ ምን ያህል አሳሳቢና መዋቅራዊ እንደሆነ ከሚያሳዩት ክስተቶች አንዱ የጋምቤላ ከተማ ፓሊስ አዛዥ መገደል ነው ተብሏል። ዛሬ የከተማው ፖሊስ አዛዥ መገደሉን ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፣ የክልሉ የጸጥታ ቢሮም ይህን መረጃ በይፋ አምኗል።
የከፍተኛ የጸጥታ አመራር መገደል በክልሉ ያለውን የደህንነት ሁኔታ መናጋት፣ የትዕዛዝ ሰንሰለት መፈራረስ እና የጥቃት ፈጻሚዎች ያላቸውን ድፍረት የሚያሳይ ነው ተብሏል። ይህ ክስተት በክልሉ የመረጋጋት ተስፋ ላይ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ ሆኗል።
የዚህ ዓይነቱ ግጭት ሰላማዊ ዜጎችን ከመጉዳት አልፎ የክልሉን አስተዳደራዊ እና የጸጥታ መዋቅሮችን እያፈረሰ ነው።
በአስቸኳይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ካልተደረገ፣ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ወደ ሰፊ የሰብአዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ነዋሪዎች አስታውቀዋል።











