ዕገዳው የተጣለባቸው አገራት 40 ደርሰዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ የአምስት አገራት ዜጎች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ መከልከላቸ
ው ይፋ ሆኗል፡፡
በዚህም መሰረት አምስት አገራት ከአፍሪቃ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ሶሪያ እና የፍልስጤም ባለስልጣናትን አካቷል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ከአፍሪቃ አገራት ቡርኪናፋሶ፣ ኒጀር፣ ማሊ፣ ሴራሊዮን እና ደቡብ ሱዳን ተካተዋል፡፡ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በከፊል በዕገዳው ተጠቃሽ የነበሩት የደቡብ እስያ አገር ላኦስ ዜጎች ሙሉ በሙሉ በዕገዳው ውስጥ ተካተዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፐ ከሁለት ቀናት አስቀድሞ በሶሪያ የተገደሉትን የአሜሪካ የጦር ኃይል አባላትን በሚመለከት የበቀል እርምጃ እንወስዳለን ማለታቸውን ተከትሎ ይህ የጉዞ ዕገዳ ተጥሎ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በተመሳሳይ ደገሞ በፍልስጤም ዜጎች በተለይም ደግ በሹማምንት ላይ የተጣለው የጉዞ ዕቀባ ከእስራኤል ጋር በተገባው ቁርሾ ነው ተብሏል፡፡
ፕሬዘዳንቱ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሲያስተላልፉ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በተለይም ከተለያዩ አገራት ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ጉዞዎችን በሚመለከት ትኩረት አድርገው ሲሰሩም ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በእስካሁኑ የነጩ ቤተ መንግስት ቆይታቸው ከአሁኑ የጉዞ ዕገዳው ጋር በጠቅላላ 40 ለሚደርሱ አገራት በሙሉ እና በከፊል እንዲሁም በየደረጃው የጉዞ ዕገዳ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሜሪካ በሚገኙ የሌላ አገር ዜጎች ላይ የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች በአገር ውስጥ ለሚገኙ ፍልሰተኞች እና የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ በሚገኙ ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ጭንቀት እና ፍርሃት ፈጥሯል፡፡ ከቀናት በፊት በ Temporary Protection Status (TPS) በአሜሪካ ሲኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት የሚመለሱበት ውሳኔ መተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በቀጣይ የጉዞ ዕገዳ ከሚጣልባቸው አገራት ውስጥ እንዳትካተት በርካታ ስራዎችን እና ግንኙነቶችን ከአሜሪካ ጋር ማጠናከር እንደሚኖርባትም በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሕግ ባለሙያዎች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡










