Home / ማህበራዊ / ፓርቲዎች አዲሱን የአየር ማረፊያ ግንባታ ተቃወሙ

ፓርቲዎች አዲሱን የአየር ማረፊያ ግንባታ ተቃወሙ

ኦነግ የአቡ ሴራ ገበሬዎች በኤርፖርት ፕሮጀክቱ ላይ የባለቤትነት ድርሻ ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እንዲሁም የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ በቢሾፍቱ አቡ ሴራ አካባቢ የሚገነባውን አዲስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ፣ አገራዊ ፕሮጄክቱ ከአካባቢው በርካታ አርሶ አደሮችን የሚያፈናቅል እንደሆነ በመግለጽ ተቃውመዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የሚፈናቀሉ ገበሬዎች በፕሮጀክቱ ላይ ቀጥተኛ የባለቤትነት ድርሻ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በጽኑ አሳስቧል።

ኦነግ በመግለጫው እንዳሰፈረው፣ መንግስት ገበሬዎቹን በጥቂት የገንዘብ ካሳ ብቻ አፈናቅሎ ከመሸኘት ይልቅ አርሶ አደሮቹና ወራሾቻቸው በቋሚነት ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና በሀብቱ ላይ ያላቸውን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ የድርሻ ወይም የሼር (Share) ስርአት ሊዘረጋላቸው ይገባል ብሏል። አርሶ አደሩን የፕሮጀክቱ አካል በማድረግ ባለቤትነቱን ማረጋገጥ እየተቻለ፣ በልማት ስም በትኖ ማስቀረት የቀድሞ ስርአቶች ሲፈጽሙት የነበረውን አድሎአዊ ተግባር እንደመቀጠል እንደሚቆጠርም ኦነግ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በስድስት ቀበሌዎች የሚገኙ ከ15,000 በላይ የቤተሰብ አባላት ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት፣ ምርታቸውን እንኳን ሳይሰበስቡና ንብረታቸውን ሳይሸጡ በዘመቻ መልክ እንዲነሱ መደረጋቸውን ድርጅቱ ገልጾ፣ እነዚህ ተፈናቃዮች በቢሾፍቱ ከተማ ዳርቻ በሚገኘው ዲባዩ በተባለ አካባቢ ቢሰፍሩም መሰረታዊ የሆኑት የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃ እና የመብራት አገልግሎቶች በአስቸኳይ ሊሟሉላቸው እንደሚገባ አሳስቧል።

ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም ተቃውሞ ቀስቅሶ የነበረው የማስተር ፕላን አካል መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ እንደ እቃ፣ ጉለሌ እና ገላን ያሉ የኦሮሞ ጎሳዎች ከቀያቸው ተነቅለው የታሪክና የባህል መጥፋት እንደደረሰባቸው ሁሉ በአቡ ሴራ ገበሬዎች ላይም ተመሳሳይ አደጋ እንዳያንዣብብ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቋል።

በተመሳሳይ ኦፌኮ በሸገር ከተማ ምስረታ እና በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የተከሰተውን መፈናቀል በሚመለከት ማስጠንቀቂያዎችን ሲሰጥ መቆየቱን አውስቶ የአሁኑ ፐሮጄክት ግን ችግሩ መባባሱን ማሳያ ነው ሲል በመግለጫው አስታውቋል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *