የወልቃይት አስተዳደር “ሕገ ወጥ ተግባራት ፈጽመዋል” ያላቸውን ሁለት አለም ዓቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
እገዳ የተጣለባቸው በአማራ ክልል ስር በሚተዳደረው አወዛጋቢው ወልቃይት የተሰማሩት International Medical Corps (IMC) እና Norwegian Refuse Council (NRC) ናቸው። አስተዳደሩ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ ሁለቱ ድርጅቶች ከተሰማሩበት ሰብዓዊ አገልግሎት ይለቅ ፖለቲካዊ ውግንና አሳይተዋል በማለት ከሷል።
ተቋማቱ ተሳትፈውባቸዋል ተብለው ለእገዳ ያበቋቸው ተግባራት ወገንተኛ የፖለቲካ አቋም መያዝ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እንደ አፈናቃይ መፈረጅና የፕሪቶሪያውን ስምምነት መጣስ ናቸው።
International Medical Corps (IMC) የተባለው ድርጅት ተሸከርካሪ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ውስጥ ተሳትፎ እንዳለው አስተዳደሩ ገልጿል። የድርጅቱ ተሽከርካሪ በጫነው የውሃ ታንከር ውስጥ ሦስት ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ደብቆ ሲያዘዋውር፣ መስከረም 29/2018 ዓ.ም በዳንሻ ከተማ መያዙን አስተዳደሩ አስታውቋል።
በአማራ እና ትግራይ ያልተፈታ የይገባኛል ጥያቄ ያለበት ወልቃይት በፕሪቶሪያው ስምምነት አወዛጋቢ ተብሎ የተገለጸ ቢሆንም፣ ሁለቱ ድርጅቶች አካባቢ የትግራይ አካል እንደሆነ አድርገው በመሳል አደናጋሪ አገላለጽ እየተጠቀሙ ነው ተብሏል። ድርጅቶቹ የወልቃይት አካባቢዎች አወዛጋቢነታቸው የታመነበት ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ የትግራይ ክልል አካል አድርገው ለይፋዊ አገላለጽ መጠቀም መቀጠላቸው የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው ብሎ እንደሚያምን አስተዳደሩ ገልጿል።
አለም ዓቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች እንዲያርሙ የተሰጣቸውን ምክረ ሀሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውም ተጠቁሟል። አስተዳደሩ የቀረበላቸውን ምክረ ሀሳብ ተቀብለው ለማረም ፈቃደኛ አይደሉም ያላቸውን ድርጅቶች፣ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በጥብቅ እሳስቧል። NRC ከዚህ ቀደም ያልተገባ እና የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ ለመጣል ተሳትፏል በሚል በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቢሮው በኢትዮጵያ መንግስት ተዘግቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።












