በደቡብ ጎንደር ዞን በደብረ ታቦር ከተማ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለረጅም ዓመታት በራዲዮሎጂ ባለሙያነት ሲያገለግሉ የነበሩት አንጋፋው ባለሙያ አቶ ሊቁ ወልዴ፣ በገና በዓል ዋዜማ በመኖሪያ ቤት አካባቢያቸው በታጠቁ ኃይሎች መገደላቸውን ተከትሎ በከተማው ነዋሪዎችና በሥራ ባልደረቦቻቸው ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ መቅሰቀሱን የሆርን ፍሪኩዌንሲ ምንጮች ገለጹ።
ግድያው የተፈጸመው በደብረ ታቦር ከተማ ቀበሌ 03 በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ ከስራ ሲመለሱ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በከተማዋ የመንግስት የጸጥታ አካላት በብዛት በሚገኙበት ሁኔታ እንዲህ አይነት ጥቃት መፈጸሙ በከተማው ያለውን የደኅንነት ስጋት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
ክስተት ተከትሎ በደብረ ታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚገኙ ሐኪሞች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ በሰጡት ቃል፣ ባልደረባቸው በታጠቁ ኃይሎች መገደላቸው ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንኳን በነፃነት መንቀሳቀስ እንዳልቻሉና “ሕይወታችን ዋስትና በሌለበት ሁኔታ ሥራችንን በአግባቡ መሥራት አልቻልንም” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ባለሙያዎቹ ለሕዝብና ለሀገር የሚቆረቆር፣ የታካሚዎችን እንግልት ለመቀነስ የኤክስሬይ ማሽን በግል ጥረቱ በማስመጣት ጭምር የሚታወቅን መልካም ሰው እንዲህ ባለ መንገድ ማጣት ትልቅ ኪሳራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለሙያው በሥራቸው ታታሪ፣ ሰው አክባሪና ሩህሩህ እንደነበሩ የጠቀሰ ሲሆን፣ ግድያውን ተከትሎ የተፈጠረው የጸጥታ ስጋት በጤና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑ ታውቋል።የጸጥታው ሁኔታ አስጊና በዚሁ ከቀጠለ ስራ ለማቆም እንገደዳለን ሲሉም የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።











