Home / ፖለቲካ / የፌደራል መንግስት ምላሽ ሊሰጠኝ አልቻለም ሲል የራያ አላማጣ አስተዳደር አስታወቀ

የፌደራል መንግስት ምላሽ ሊሰጠኝ አልቻለም ሲል የራያ አላማጣ አስተዳደር አስታወቀ

ከሰሞኑ በህወሃት ኃይሎች እና በትግራይ የሰላም ኃይሎች በተባሉ ቡድኖች መካከል የተከሰተውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ በራያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚመለከት ከመንግስት ምላሽ ማጣታቸውን የራያ አላማጣ ከንቲባ አቶ ሃይሉ አበራ ለሆርን ፍሪኩዮንሲ ገለጹ።

ከትላንት ወዲያ በራያ አዘቦ አካባቢ ሃራ መሬት የሰላም ሰራዊት የሚባለው ሃይልና በሕወሃት ሃይል መካከል ተኩስ ተቀስቅሶ እንደነበር ገልጸው፤ ይህም ተኩስ ተስፋፍቶ በራያ አላማጣ ህዝብ ላይ ትልቅ ሽብር ፈጥሮ እንደነበር አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ህጋዊነቱን የሠረዘው ሕወሓት በኃይል ወደ ትግራይ ጠቅልሎ ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በራያ ህዝብ ላይ ግፍ እየፈፀመ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የፌደራል መንግስት ኮማንድ ፖስት ባለበት ቀጠና እነዚህ ጥሰቶች እየተፈጸሙ ለእነዚህ በደሎች ‘ባላየ’ ማለፉን ከንቲባው ገልጸዋል።

ከተጠቀሱት ከባድ ጥሰቶች መካከል በአላማጣና ራያ ባላ ወረዳዎች 11 ሰዎች መገደላቸው፣ 249 ሰዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙ እንዲሁም 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት እና የንግድ ዕቃዎች ዝርፊያ መድረሱን ነግረውናል።

በተጨማሪም ከ55,000 በላይ ህዝብ መፈናቀሉ፣ ከ60,000 በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው፣ እና ከፍተኛ ህገወጥ የመሬት ወረራና የደን ጭፍጨፋ እየተፈጸመ መሆኑ አክለዋል። ይህ በደል በቂ ምላሽ ባለማግኘቱ የአካባቢው ኮሚቴ ለፌደራል መንግስት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቋል ብለዋል።

በዋናነት የሕወሃት ሠራዊት የማንነት ጥያቄ ካላቸው የራያ ወረዳዎች ያለ ቅድመ ሁኔታ ለቀው እንዲወጡ እንዲደረግ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲተገበርና ግዚያዊ አስተዳደር በቀጥታ በህዝቡ እንዲመረጥ እንዲሁም የኮማንድ ፖስቱ ተልዕኮ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ የሚያዝ ደብዳቤ ለመንግስት ማስገባታቸውን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለራያ ህዝብ ድምፅ ባለመሆኑ ቅሬታውን ገልጾ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የራያ ህዝብ ጥያቄ የማንነትና የህልውና እንጂ የስልጣን ጥያቄ ባለመሆኑ ድምፅ እንዲሆኑለት ጥሪ አቅርቧል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *