Home / ቢዝነስ / የዘገየው የደመወዝ ጭማሪ በአስቸኳይ እንዲከፍል ትዕዛዝ ተሰጥቷል

የዘገየው የደመወዝ ጭማሪ በአስቸኳይ እንዲከፍል ትዕዛዝ ተሰጥቷል

የአንድ ወር ጭማሪ 9 ቢሊዮን ብር ነው

መንግሥት ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ያለው የደመወዝ መዘግየት፣ በሰራተኛው ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ተከትሎ በገንዘብ ሚኒስቴር ትዕዛዝ በአስቸኳይ ክፍያ እየተፈጸመ መሆኑን ረተድተናል።

ከመስከረም 1/2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የደመወዝ ጭማሪ የተጓተተው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የውሳኔ መዘግየት ነው ተብሏል።

በእርግጠኝነት ሲጠብቅ የነበረው የደመወዝ ጭማሪ በመስከረም ወር ተግባራዊ አለመሆኑን ተከትሎ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች መንግሥት ሰራተኛው ቅሬታ ውስጥ ገብቷል። ይሄንኑ የደመወዝ መዘግየት የፈጠረው ቅሬታ እንዳይስፋፋ በሚል፣ በጥቅምት ወር ሊከፈል የነበረው ጭማሪ ደመወዝ በጥቅም አጋማሽ እየተከፈለ ነው።

ለመዘግቱ ምክንያት ነው የተባለው ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ገንዘብ ሚኒስቴር ተጨማሪ የደመወዝ በጀቱን ለቋል። ገንዘብ ሚኒስቴር የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ውሳኔ እንደደረሰው ብሔራዊ ባንክ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመስከረም ወር ተጨማሪ ደመወዝ በጀት እንዲለቅ የጠየቀበትን ደብዳቤ ተመልክተናል።

የመስከረም ወር አጠቃላይ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተጨማሪ በጀት ዘጠኝ ቢሊዮን ብር መሆኑ በደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዘገየውን ጭማሪ የጥቅምት ወር ደመወዝ ሳይደርስ እንዲከፍሉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥራቸው በጀት ገብቶላቸዋል።

ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የደረሳቸው ትዕዛዝ መሰረት አድርገው ጭማሪው መክፈል ጀምረዋል። ለአብነትም 640 ሚሊዮን ብር የተበጀተለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስከረም ወር ጭማሪ ደመወዝ መከፈሉ ከመንግሥት ሰራተኞች ሰምተናል።

የመስከረም ወር የደመወዝ ጭማሪ ከፍተኛ በጀት ያገኘው ኦሮሚያ ክልል ሲሆን፣ 2.6 ቢሊዮን ብር ተለቆለታል። በሁለተኛው ደግሞ አማራ ክልል ሁለት ቢሊዮን ብር እንደተለቀቀለት ዝግጅት ክፍላችን የተመለከተው የበጀት ድልድል ሰነድ ያመላክታል።

ዝቅተኛ የተጨማሪ ደመወዝ በጀት የተበጀተላቸው ደግሞ ሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ናቸው። ሐረሪ ክልል 54 ሚሊዮን ብር ሲበጀትለት፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 61 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል።

መንግሥት ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ፣ የተፈጠውን የኑሮ ጫና ለማቃለለት የሰራተኛውን ኑሮ ለመደጎም ደመወዝ ጭማሪ ማድረጉ ይታወሳል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *