Home / ቢዝነስ / አሻም ቲቪ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ የግብር ጫና መዘጋቱ ታወቀ

አሻም ቲቪ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ የግብር ጫና መዘጋቱ ታወቀ

ለተከታታይ ስምንት ዓመታት የተለያዩ መረጃዎችን ለሕዝብ በማድረስ ሰፊ ተደራሽነት የነበረውና በቅርቡ ከሳታላይት የወረደው አሻም ቲቪ ሙሉ በሙሉ የተዘጋው መንግሥት ባቀረበበት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የግብር ጫና መሆኑን ምንጮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አስታውቀዋል።

ጣቢያው በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮና በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር በቀረበበት ተደራራቢ የግብር ጫና መዘጋቱን ሆርን ፍሪኩዌንሲ ለጉዳዩ ቅርቀት ካላቸው ምንጮች ሰምቷል።

ምንም እንኳን ጣቢያው በየዓመቱ ግብር ሲከፍል የነበረ ቢሆንም፣ ገቢዎች ሚኒስቴር የ15 ሚሊዮን ብር የግብር ክስ አቅርቦበታል። ገቢዎች በአግባቡ አልተከፈለኝም ያለውን 15 ሚሊዮን ብር ጣቢያው እንዲከፍለው በፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ጉዳዩ በሂደት ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ ጣቢያው በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሰባት ሚሊዮን ብር የግብር ክስ ቀርቦበታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የጣቢያውን አንድ ተሽከርካሪ በመያዣነት መውሰዱን ምንጮች ገልጸዋል።

ጣቢያው በመንግሥት ከቀረበበት ግብር በተጨማሪ፣ በሰራተኞች የደመወዝ ክስ ተመስርቶበታል። ተሰናባች ሰራተኞች የሥራ መፈለጊያ ደመወዝ እንዲከፈላቸው በፍርድ ቤት ክስ አቅርበው በመከራከር ላይ እንደሚገኙም ዝግጅት ክፍላችን የደረሰው መረጃ ያመላክታል።

ቀድሞውኑ ከወጪው ጋር የሚመጣጠን ገቢ ያልነበረው ቴሌቪዥን ጣቢያው፣ የቀረበበትን ተደራራቢ የግብር ክስ ተቋቁሞ መቀጠል አልቻለም ሲሉም ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል። የጣቢያው ባለቤቶች ባለፉት ተከታታይ ሁለት ዓመታት ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ ውስጥ መግባታቸውን ዝግጅት ክፍላችን ተረድቷል።

በኢትዮጵያ መረጃና ቁምነገር ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተከታታይነት እየተዘጉ ነው። እንደ አሐዱ፣ ናሁ፣ ባላገሩ፣ ቲቪ ዘጠኝ፣ ኢሳት፣ አፍሮ ኒውስ ያሉ መረጃና ቁምነገር ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ጣቢያዎች ከሳታላይት መውረዳቸው ሰራተኞቻቸውን በትነው መዘጋታቸው የሚታወስ ነው፡፡

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *