በጋምቤላ ክልል ውስጥ ከሰሞኑ በታጠቁ አካላት በተፈጸመው የሽብር ጥቃት የተቀሰቀሰው ግጭትና ውጥረት ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የከተማዋ አስተዳደር አስቸኳይ የጸጥታ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታውቋል የእንቅስቃሴ ገደብም ተጥሏል፡፡
ይህ ውጥረት በክልሉ በሚገኙ በኑዌርና በአኝዋክ ብሔረሰቦች መካከል ከፍተኛ ስጋት እንዲነግስ አድርጓል።
በጋምቤላ ከተማ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም የታጠቁና የክልሉን ፖሊስ ልብስ የለበሱ አካላት በመኪና ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ንጹሐን ላይ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ከፍተው በርካታ ሰዎችን ለሞትና ለመቁሰል መዳረጋቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ግጭት እስካሁን መፍትሄ አላገኘም ብለዋል።
የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕዴን) ሊቀመንበር አቶ ሳይመን ቱት፣ ይህ ድርጊት ቀደም ሲል ጋብ ብሎ የቆየውን ግጭት ዳግም ለመቀስቀስ ታስቦበት የተፈጸመ የሽብር ጥቃት መሆኑን አረጋግጠዋል። ጥቃቱን ተከትሎ የጋምቤላ ከተማ ከጸጥታ አካላት ውጭ ማንኛውም ተሽከርካሪና ሰው ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ መንቀሳቀስ እንዳይችል ተደርጓል። ውጥረቱ በመባባሱ ምክንያት፣ የከተማዋ አመራሮች የጸጥታ ሁኔታውን ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ ትኩረት ያደረገ አስቸኳይ ውይይት እያካሄዱ ነው ተብሏል።
የጋምቤላ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ጉደታ እንደተናገሩት፣ አመራሮች በተከሰተው የጸጥታ አለመረጋጋት ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል።
አመራሮቹ በቀበሌ ደረጃ ወርደው ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት በማካሄድ የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩ የስራ መመሪያ ተሰጥቷል። አቶ ማርቆስ ጉደታ አክለውም፣ ችግር እየፈጠሩ ያሉት ውስን ግለሰቦች ስለሆኑ አብዛኛው የጋምቤላ ከተማ ሰላም ወዳድ ማህበረሰብ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የሰላሙ ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።
በውይይቱ ላይ የጸጥታ አካላት የማረጋጋት ስራ እያከናወኑ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የከተማው ነዋሪዎች መደበኛ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳለባቸው ተገልጿል።
ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ፣ እንዲሁም በከተማው የሚገኙ የንግድ ተቋማት ክፍት ሆነው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።
ቢሆንም ግን በምሽት ወቅት በከተማዋ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት፣ ከጸጥታ አካላት ውጭ ማንኛውም ተሽከርካሪና ሰው ከትላንት ሕዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት 1:00 ጀምሮ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑ ተገልጿል።










