Home / ማህበራዊ / ‹‹የትምህርት አይነቶች መታጠፍ በርካታ መምህራንን ስራ ሊያሳጣ ይችላል›› የመምህራን ማኅበር

‹‹የትምህርት አይነቶች መታጠፍ በርካታ መምህራንን ስራ ሊያሳጣ ይችላል›› የመምህራን ማኅበር

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በርካታ የትምህርት አይነቶች እንዲሰረዙ ወይም እንዲጠቃለሉ መወሰኑ፣ ለዓመታት ሲያስተምሩ የቆዩ መምህራንን ከስራ ገበታቸው ሊያፈናቅላቸው እንደሚችል ተገለጸ።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በጉዳዩ ላይ ስጋቱን የገለጸ ሲሆን፤ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ መምህራን እና ቤተሰቦቻቸውን የተጋረጠባቸውን ችግር በአደባባይ ተናግሯል። ኢመማ ምክትል ፕሬዝደንት ሽመልስ አበበ እንደገልጹት፣ የትምህርት ሚኒስቴር ‘ተበታትነው የቆዩ የትምህርት አይነቶችን በአንድ የማጠቃለል’ ውሳኔ፣ በርካታ መምህራንን የስራ ገበታቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል ብለዋል።

“ከአቅም በላይ የሆኑ በርካታ ቅሬታዎች ደርሰውናል፤ መምህራን ‘ነገ ምን እንሆናለን?’ የሚለው ፍርሃት አንገታቸውን አስደፍቷል። መንግስት ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ የበርካታ መምህራንን እና ቤተሰቦቻቸውን ህልውና ችላ ማለት የለበትም” ሲሉ ገልጸዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ ለሥራ እጦት የተጋለጡትን መምህራን ትክክለኛ ቁጥር ለመግለጽ ባይችሉም፣ የደረሳቸው የቅሬታ መጠን ውሳኔው ሰፊ ቁጥር ያላቸውን መምህራን ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን እንደሚያመለክት ተናግረዋል፡፡

የማህበሩ አመራሮች እንደሚሉት፣ የትምህርት አይነቶችን ማሻሻል ወይም ማጠፍ የተለመደ የመንግስት አሰራር ቢሆንም፣ ይህ ሂደት የትምህርቱን አሰጣጥ ከማሻሻል ባሻገር መምህራንን ያላገናዘበ እና የቤተሰብ አስተዳዳሪዎችን ለስራ አጥነት የሚዳርግ በመሆኑ አግባብነት የለውም ብለዋል።

በርካታ ኃላፊነት ያለባቸው መምህራን በድንገተኛ የመንግስት ውሳኔ ምክንያት ስራ አጥ ሆነው መንገድ ላይ መውጣት የለባቸውም ሲልም ማኅበሩ ተናግሯል፡፡ መንግስት የጀመረውን ውሳኔ ሰብአዊነት ባለው መንገድ የመከለስ እና የመፍትሄ አማራጮችን የመዘርጋት ሃላፊነት እንዳለበት ተጠቁሟል።

ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ውሳኔው መምህራንን ሥራ ከማሳጣት ጋር የሚያያዝ ሳይሆን፣ የትምህርት ጥራትን እና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ከጊዜያት በፊት ገልጾ ነበር። በተጨማሪም ውሳኔው የመጣው የሀገሪቱን የትምህርት ስርዓት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና ለሥራ ገበያው ተወዳዳሪ ለማድረግ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

“ቀደም ሲል በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው የትምህርት አይነቶች ተበታትነው ይሰጡ ነበር። ይህ ደግሞ በሀብት በጊዜ፣ በሰው ኃይል እና በገንዘብ ላይ ብክነት ከመፍጠሩም በላይ፣ ተማሪዎች የሚያገኙት እውቀት ትኩረት የለሽና ቀጥተኛ ያልሆነ እንዲሆን አድርጎ ነበር” ሲሉ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ቀደም ሲል በሰጡት ማብራሪያ ላይ መጠቀሱ የሚታወስ ነው።

ሚንስቴሩ የመምህራንን ስጋት ሙሉ ለሙሉ ችላ እንደማይል በመጠቆም፣ ለስራ እጦት እንዳይጋለጡ አማራጮችን እንደሚጠቀም ሲያስታውቅ ቢቆይም የመምህራን ስጋት ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *