መንግሥት በነዳጅ ምርቶች ላይ የጣለው የ30 በመቶ እሴትና ኤክሳይዝ ታክስ ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል መባሉን ተከትሎ፣ ማደያዎች ከጭማሪው ለማትረፍ ነዳጅ እየደበቁ እንደሆነ እና ይህንንም ተከትሎ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በነዳጅ ዋጋ ላይ መታየቱን ሆርን ፍሪኩዌንሲ አረጋግጧል፡፡
የነዳጅ ማደያዎች ከወዲሁ ነዳጅ የለንም በማለት የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት ማድረጋቸው ሆርን ፍሪኩዌንሲ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች ገልጸዋል። ከአንድ ሳምንት ወዲህ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች፣ በአንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎች ተከሰቷል።
ማደያዎች ነዳጅ የለንም ማለታቸው ተከትሎ፣ ከመደበኛው ዋጋ ከእጥፍ በላይ የሚሸጥበት የኮንትሮባንድ ገበያው ደርቷል። ወትሮውንም ነድጅ በኮንትሮባንድ በሚሸጥባቸው እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ባሉ አካባቢዎች፣ በሕገ ወጥ መንገድ ነዳጅ በሊትር እስከ 500 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው።
አንዳንድ ማደያዎች ነዳጅ የለንም ካሉ በኋላ በድብቅ እስከ 50 በመቶ ዋጋ ጨምረው እንደመሸጡ አሽከርካሪዎች ጠቁመዋል።
መንግሥት በነዳጅ ምርቶች ላይ የጣለውን 15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና 15 በመቶ ኤክሳይዝ፣ አጠቃላይ 30 በመቶ ግብር በመጪው ታህሳስ ወር ተግባራዊ ለማድረግ አቅዷል። ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የ30 በመቶ ግብር ከነዳጅ ምርቶች ላይ ሰብስቦ፣ ለመንግሥት ገቢ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል።









