የድሞዝ ጥያቄ ያነሱ መምህራንን ማሰር ተጀምሯል
በሰሜን ጎንደር ዞን በአዳርቃይ ወረዳ የሚገኙ መምህራን የመስከረም ወር ደመወዛቸው ባለመከፈሉ ምክንያት ባካሄዱት የስራ ማቆም አድማ ምክንያት ከ1-12ኛ ክፍል ከዛሬ ጀምሮ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሙሉ በሙሉ ማቋረጣቸውን ለሆርን ፍሪኩዮንሲ ገልጸዋል።
መምህራኑ ለሆርን ፍሪኩዮንሲ እንደገልጹት፤ የመስከረም ወር ውዝፍ ደመወዛቸው እንዲከፈል በተደጋጋሚ የወረዳውን ትምህርት ጽ/ቤት ቢያነጋገሩም ተጨባጭ ምላሽ ማግኘት ብለመቻላቸው አድማውን ማካሄዳቸው ታውቋል፡፡
ደመወዝ የኑሯቸው ዋነኛ መሠረት በመሆኑ፣ ክፍያው መጓደሉ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የስነ-ልቦና ጫና እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ። ለወር ሙሉ ላከናወነው ሥራ ክፍያ ማጣት ማለት የቤተሰብን ፍላጎት ማስተናገድ አለመቻል፣ የቤት ኪራይ መክፈል አለመቻል እና ለመሠረታዊ ነገሮች የሚሆን ገንዘብ ማጣት ማለት ነው ሲሉም መምህራን ይናገራሉ፡፡
በዚህ ስቃይ ውስጥ ሆነው ተረጋግተው ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት ባለመቻላቸው፣ ሌላ አማራጭም ስላላገኙ የስራ ማቆም አድማውን ማወጃቸውን ገልጸዋል።
የአዳርቃይ ወረዳ ቀደም ሲልም በፀጥታ ችግር ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሲስተጓጎል መቆየቱ የሚታወስ ነው። በአሁኑ የደመወዝ አለመክፈል ችግር ምክንያት ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው ትምህርት ሙሉ በሙሉ መቋረጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የወደፊት ዕጣ አደጋ ላይ ጥሏል። ተማሪዎች ቀደም ሲል በፀጥታ ምክንያት ያጡትን የመማሪያ ጊዜ ለማካካስ በሚሞከርበት በዚህ ወቅት፣ በድጋሚ ትምህርት መቋረጡ ውጤታማነታቸውን በእጅጉ እንደሚጎዳ ተመላክቷል።
የክፍል ደረጃ ፈተናዎች እና የብሔራዊ ፈተናዎች ጊዜ እየተቃረበ ባለበት ወቅት፣ መቆራረጡ ተማሪዎች አስፈላጊውን ዕውቀት እንዳያገኙ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
በወረዳው የትምህርት ጽ/ቤት ውስጥ የስርዓተ ትምህርት ቡድን መሪ የሆኑት ግዛቸው ጌታነህ ክፍያው መጓደሉን አረጋግጠው፤ ችግሩ የተፈጠረው የበጀት እጥረት በማጋጠሙ እንጂ ክፍያ አንከፍልም የሚል አቋም እንዳልተወሰደ ገልጸው፣ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በስፋት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ማብራሪያ መምህራኑን አላረካም፤ መፍትሔው ተጨባጭ እርምጃ እና የደመወዝ ክፍያ እንጂ ማብራሪያ ብቻ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። በተጨማሪም የአድርቃይ ወረዳ አስተዳዳሪ ደሳለኝ አባተ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት «የበጀት እጥረት አጋጥሞን ነው ያልከፈልነው። ከወረዳው ያለንን ጥሬ ገንዘብ ለማከፋፈል አስበን ነበር የጥሬ ገንዘብ እጥረት በእጅጉ አጋጥሞናል» ብለዋል።
የወረዳው የመንግስት አካላት ይህን ይበሉ እንጂ የደሞዝ ጥያቄ ያነሱ መምህራን ለእስር እና እንግልት እየተዳረጉ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል።
በአዳርቃይ ወረዳ ትምህርት የተቋረጠበት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው የዞንና የክልል አካላት የመምህራንን ስቃይ ተረድተው የተማሪዎችን የትምህርት መብት በአስቸኳይ ለማስጠበቅ የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቧል።









