Home / ቢዝነስ / የከተማ አውቶብስ ክፍያ በእጥፍ መጨመሩን ተከትሎ የህዝብ ቅሬታና ሮሮ ቀጥሏል

የከተማ አውቶብስ ክፍያ በእጥፍ መጨመሩን ተከትሎ የህዝብ ቅሬታና ሮሮ ቀጥሏል

መንግስት የተደረገ ጭማሪ የለም ብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚተዳደሩት የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት እና ሌሎች ፐብሊክ ባሶች የትራንስፖርት ክፍያ ታሪፍን በድንገት በእጥፍ በማሳደጋቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ሮሮ አስነስቷል።

በደረሰን መረጃ መሰረት፤ የሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቹ ምንም ዓይነት ይፋዊ ማስታወቂያ ወይም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጡ፣ በዚህ ሳምንት ብቻ 10 ብር የነበረውን ታሪፍ ወደ 20 ብር ከፍ አድርገው ማስከፈል መጀመራቸው ተረጋግጧል።

ይህ የእጥፍ ጭማሪ በተለይም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩትን የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫና በእጅጉ አባብሶታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ምክንያት የኑሮ ውድነት እንዳይባባስ እና የትራንስፖርት ክፍያ እንዳይጨምር እየሰራን ነው የሚል መግለጫ ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም አስቀድሞ የራሱ የከተማ አስተዳደሩ በሚያስተዳድረው የትራንስፖርት ዘርፍ ታሪፉን በእጥፍ ማሳደጉ፣ የከተማ አስተዳደሩ የሰጠው ቃል እና በተግባር የታየው ድርጊት በእጅጉ የተራራቀ መሆኑን ያሳያል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ሲገልጹ፣ “የመንግስት ባሶች የተመጣጣኝ ዋጋ አማራጭ ሆነው መቅረብ ሲገባቸው፣ አሁን ላይ ከግል ትራንስፖርቶች የማይተናነስ አልያም የሚበልጥ ክፍያ ማስከፈል መጀመራቸው በፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

በተለይ በዕለት ተዕለት ውሎአቸው ለስራ እና ለትምህርት በመንግስት የሕዝብ ማመላለሻዎች ላይ ጥገኛ የሆኑ ዜጎች፣ በቀን 20 ብር ይከፍሉበት የነበረው የጉዞ ወጪ ወደ 40 ብር ማደጉ በወር ከ 600 ብር በላይ የሚሆን ተጨማሪ የትራንስፖርት ወጪያቸው ላይ መጫኑንና ይህም ለሌላው የኑሮ ፍጆታቸው መሸፈኛ የሚሆን ገንዘብ እንዲያጡ እንዳደረጋቸው አስታውቀዋል።

“የደመወዝ ጭማሪ ተደረገ ተብሎ የሚነገረው ወሬ፣ ኑሮአችንን ሳይሆን የባስ ታሪፍን ነው የጨመረው” የሚል መራር አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎችም ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ክፍያ ጭማሪውን አስመልክቶ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ይፋዊ ማብራሪያ ያልሰጠ ሲሆን፣ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች የትራንስፖርት ታሪፉ በአስቸኳይ እንዲታይ እና የእጥፍ ጭማሪው ተገቢው ድጎማ ታክሎበት ወደ ቀድሞ ዋጋው እንዲመለስ ጥሪ አቅርበዋል።

በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ድርጅት የአገልግሎት ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ከበደ ለሆርን ፍሪኩዌንሲ እንደገለጹት የተነገረው ጭማሪ ሐሰት መሆኑን እና በህዝብ ማመላለሻ ባሶች ላይ የተጨመረ ምንም አይነት የታሪፍ ጭማሪ የለም ሲሉ ተናግረል፡፡

የአገልግሎት ተጠቃሚዎች ደግሞ ከተለመደው ታሪፍ በላይ እጥፉን እየከፈልን ነው ማለታቸውን ቀጥለዋል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *