የመንግሥት ሰራተኞችን ደመወዝ ከሕግ አግባብ ውጭ መቁረጥ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል።
ተቋሙ በጉዳዩ ላይ ባወጣው ሪፖርት በተለያዩ አካባቢዎች ከሕግ አግባብ ውጪ የደመወዝ መቁረጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ በመቀጠሉ “የአስተዳደር በደል” አስከትሏል ብሏል። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በፍርድ ቤት ከሚሰጥ ትዕዛዝ ወይንም በሕግ በግልጽ ከተደነገገው አሰራር ውጭ ከሰራተኞች ደሞዝ መቁረጣቸው ባደረገው ክትትል መረዳቱን ተቋሙ ገልጿል።
ዕንባ ጠባቂ በሪፖርቱ የመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ ከሕግ አግባብ ውጭ ያለ ፈቃደኝነት መቁረጥ የአስተዳደር ‘በደል’ ነው ብሏል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመንግሥት ሰራተኞች ለተለያዩ ስራዎች በሚል ደመወዛችን ያለ ፈቃዳቸው እንደሚቆረጥበቸው ቅሬታ እንዳቀርቡለት ተቋሙ አመላክቷል። ለአብነትም በሲዳማ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ በርካታ መምህራን፤ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ሰራተኞች ፈቃዳቸውን ሳይሰጡ ከደመወዛቸው ላይ እየተቆረጠባቸው መሆኑን በመግለጽ መፍትሄ እንዲሰጣቸው በተለያዩ ጊዜያት ለተቋሙ አዋሳ ቅርንጫፍ አቅርበዋል ተብሏል።
በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ መምህራን ተመሳሳይ ቅሬታ ማቅረባቸውም ተገልጿል። ዕምባ ጠባቂ ተቋሙ የቀረቡለት ከደመወዝ መቆረጥ ጋር የተገናኙ ቅሬታዎች መደራረብ፣ ችግሩ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ አመላካች መሆኑን ጠቁሟል።
የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 ዓ.ም በአንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ (2) ላይ የመንግሥት ሰራተኛ ደመወዝ የሚቆረጥበት አግባብ በግልጽ ደንግጓል። ማንኛውም ሰራተኛ ደመወዙ የሚቆረጠው ስምምነቱን በጽሑፍ ሲገልጽ፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወደም በሕግ በተደነገገው አሰራር መሆኑ በአዋጁ ተጠቅሷል።
በአዋጁ ከተደነገገው አሰራር ውጭ የሰራተኞች ደመወዝ ሊያዝ ወደም ሊቆረጥ እንደማችል ተደንግጓል። በዚሁ ንዑስ አንቀጽ (ሰ) ወይም (ሐ) መሠረት ከሠራተኛ ደመወዝ በየወሩ የሚቆረጠው ከደመወዙ አንድ ሦስተኛ እንደማደበልጥ በንኡስ አንቀጽ ላይ በግልጽ ተደንግጓል። ምንም እንኳን የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ያለ ሰራተኛው ፈቃድ ወይም የሕግ አግባብ ደመወዝ የመቁረጥ ሥልጣን ባይኖራቸውም፣ የሰራተኞች መብት በግልጽ ተጥሶ ድርጊቱ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን ተቋሙ አስታውቋል።
የሰራተኞች ደመወዝ ከሕግ አግባብ ውጭ መቁረጥ በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋጅ ቁጥር 1307/2016 ዓ/ም መሰረት “አስተዳደር በደል” መሆኑ ተመላክቷል።
ከሕግ አግባብ ውጭ የሰራተኛ ደመወዝ በተቆረጠባቸው አካባቢዎች ሁሉ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተገቢው እርምት ሊደረግ ይገባል ሲል ተቋሙ አሳስቧል። የመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ መቆረጥ በሁሉም አካባቢዎች የሚነሳ ችግር ቢሆንም፣ በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የከፋ መሆኑ ይነገራል።
ሰራተኞች ለገዥው ብልጽግና ፓርቲ ህንጻ ግንባታ ጭምር ያለፈቃዳቸው ደመወዛቸው እንደሚቆረጥባቸው ይገልጻሉ። የመንግሥት አካላት የሰራተኛው በሕግ የተደነገገ መብት በግልጽ ከመጣሳቸው ሻገር፣ ቅሬታ ባቀረቡት ላይ እስርና ወከባ መፍጠራቸው መዘገቡ ይታወሳል።









