የ123 የጥቁር ገበያ ተዋንያን የባንክ ሂሳብ ታገደ
በአዲስ አበባ የተለያዩ ባንኮች ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ከጥቁር ገበያ ጋር በተያያዘ ሰፊ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የፋይናንሻል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ አስታውቋል፡፡
በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር የተጠረጠሩ 123 ሰዎች የባንክ ሂሳብ መታገዱን ተከትሎ በዝውውሩ ውስጥ የባንክ ሰራተኞችም ዕጃቸው እንዳለበት በመጠርጠሩ የተጠናከረ ምርመራ መጀመሩ ተነግሯል፡፡
በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ተዋንያንን የባንክ ሂሳብ ለማገድ ሰፊ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ሆርን ፍሪኩዌንሲ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል። ብሔራዊ ባንክ እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በሁሉም ባንኮች ላይ ለሳምንት ሰፊ ክትትል ካደረጉ በኋላ ነው የጥቁር ገበያ አዘዋዋሪዎች ናቸው የተባሉ ግለሰቦችን የባንክ ሂሳብ ያገደው።
የባንክ ሂሳባቸው የታገደ ሰዎች በተለያየ ደረጀ በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ተሳትፎ አላቸው የተባለ ሲሆን፣ የሕግ ተጠያቂነት ይጠብቅባቸዋል ተብሏል። ተጠርጣሪዎቹ በቀጣይ በሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀል ክስ እንደሚመሰረትባቸው አገልግሎቱ አስታውቋል።
ከአንድ ወር ገደማ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ለ138 የጥቁር ገበያ አዘዋዋሪዎች የባንክ ሂሳብ መታገዱ ይታወሳል። የጥቁር ገበያ ተዋንያን የባንክ ሂሳብ የታገደው ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዋን ገበያ መር ካደረገች በኋላም ልዩነቱ እየሰፋ መቀጠሉን ተከትሎ ነው።
ብሔራዊ ባንክ ከአንድ ወር ገደማ በፊት በወሰደው እርምጃ መረጋጋት አሳይቶ የነበረው የጥቁር ገበያ ዋጋ ዳግም እያሰራራ መሆኑን ሆርን ፎሪኩዌንሲ ባደረገው ክትትል ተረድቷል። ወደ 160 ብር ወርዶ የነበረው የአንድ ዶላር ምንዛሪ በአሁኑ ወቅት ወደ 164 ብር ከፍ ብሏል።










