ባሳለፍነው ወር ሐምሌ 14/2018 በኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ማዕከላዊ ኮሚቴው ያወጣውን መግለጫ እና መግለጫውንም ፓርቲው እንዲያወጣ በማድረግ ረገድ መንግስት በገንዘብ እንደደገፈው እና ለዚህም ደግሞ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለፓርቲው እንደተሰጠው ምንጮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ተናግረዋል፡፡
ምንጮች አክለውም እንደተናገሩት ኦፌኮ ይህን መግለጫ ማለትም በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት እንዲመጡ በይፋ የጠየቀበትን መግለጫ በሚመለከት ከመንግስት 10 ሚልዮን ብር መቀበሉን ገልፀዋል፡፡ ፓርቲው በተጠቀሰው ቀን በማዕከላዊ ኮሚቴው አማካኝነት በሰጠው መግለጫ ላይ መንግስትን በግልፅ መኮነኑ እና መንግሥት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን በዘዴ ማፍረሱን የገለጸ ቢሆንም ከዛ አስቀድሞ የፓርቲው ላይኛው አመራር ስብሰባ እንዲቀመጠ እና ይህንንም መግለጫ እንዲያወጣ ከመንግስት ምንም አይነት ርዕስ ያልተሰጠው የ10 ሚልዮን ብር ድጋፍ ማግኘቱን የዝግጅት ክፍላችን ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ፓርቲው በመግለጫው መንግስት ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማፍረሱን እንደማሳያ ከተጠቀመባቸው መንገዶችም ጋዜጠኞችን፣ የማሕበረሰብ አንቂዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ማሰር መሰወር እንዲሁም መግደሉን በይፋ መጠቀሱ የሚታወስ ነው፡፡
ከስብሰባው አስቀድሞ በአንድ የዜና አውታር በተገለፀ እና የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሁሉን አቀፍ ድርድር ሊደረግ መሆኑን በተሰራጬ መረጃ ዙሪያ የቀድሞው የኦፌኮ አባል ጃዋር መሐመድ የመንግስት የከፋፍሎ የመግዛት ሰልት እና ጊዜ መግዣ ሀሳብ ነው ሲሉም በፌስቡክ ገጻቸው አስነብበው ነበር፡፡ ፖለቲከኛው አያይዘውም ይህን አይነት አካሄድ የሚሰራው አሁን ካለው አስተዳደር ለውጥ በኋላ እንደሆነም ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሆርን ፍሪኩዌንሲ ከኦፌኮ በኩል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡











