አንጋፋው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሐመድ እና ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ ከቀናት በፊት በደኅንነት አካላት ተይዘው መወሰዳቸው እና እሰካሁንም የደረሱበት እንደማይታወቅ እና ፍርድ ቤትም እንዳልቀረቡ የሆርን ፍሪኩዌንሲ ምንጮች አስታወቁ፡፡
ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሐመድ ሰኞ ነሐሴ 5/2017 ቀን ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታፍኖ መወሰዱ የታወቀ ሲሆን ከቆይታ በኋላ ግን በመንግስት የደኅንነት ኃይሎች እንደተያዘ ታውቋል፡፡ በተመሳሳይም የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ ዮናስ አማረም ሐሙስ ነሐሴ 8/2017 ከቢሮ እንደወጣ በመንግስት የደኅንነት ኃይሎች ተይዞ መወሰዱን ምንቾች ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡ ምንም እንኳን ጋዜጠኞች በመንግስት የደኅንነት አካላት ተይዘው ,ቢወሰዱም ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ድረስ ያሉበት ስፍራ እንደማይታወቅ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውም በጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ለሆርን ፍሪኩዌንሲ የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡ በተለይም ደግሞ የአብዱልሰመድ ባለቤት ልጇን ከተገላገለች ጥቂት ቀናት በመሆኑ በአራስ አቅም በየፖሊስ ጣቢያው ለመዞር እንደተገደደች ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ በሪፖርተር ጋዜጣ በርካታ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ዘገባዎችን እንዲሁም ቃለ ምልልሶችን በማድረግ የሚታወቅ ሲሆን ጋዜጠኛ አብዱልሰመድም በአሐዱ ራዲዮ ቀዳሜ ገበያ የተሰኘ ፕሮግራም በማዘጋጀት ለአድማጭ ሲደርስ ቆይቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ራዲዮ ሲያገለግል እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡
ጋዜጠኞች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዘፈቀደ እስር፣ ገድያ እና እንገልት መዳረጋቸው የተለመደ ጉዳይ መሆኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ይህንም በመሸሽ በርካታ ጋዜጠኞች በስደት በተለያዩ አገራት ይገኛሉ፡፡












