የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አንድ ሰራተኛው በሰብዓዊ አገልግሎት ስምሪት ላይ እያለ ያልታወቀ ቡድን ባላቸው ጥቃት አድራሾች በተፈጸመበት ጥቃት እንደተገደለበት አስታውቋል።
ማኅበሩ ሆነልኝ ፋንታሁን የተባለ ሰራተኛው ‘አሰቃቂ’ ባለው ጥቃት መገደሉን ባወጣው የሐዘን መግለጫ አስታውቋል።
የቀይ መስቀል ሰራተኛው የተገደለው ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም ከደባርቅ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ፣ ልዩ ስሙ ጨነቅ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ለሰብዓዊ አገልግሎት ስምሪት ላይ ሳለ ታግቶ መሆኑን ማኅበሩ ገልጿል።
ማኅበሩ ማንነቱ ባልታወቀ ቡድን ተፈጽሟል ባለው እገታ ሰራተኛው፤ በተፈጸመበት ድብደባ እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ምክንያት በማግስቱ ነሐሴ 9ቀን/2017 ዓ.ም ህይወቱ ማለፉን ጠቁሟል።
ከተገደለው ሰራተኛ ጋር አብረውት በስራ ላይ የነበሩ ሁለት የማኅበሩ ባልደረቦች ከእገታ ተርፈዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሁሉም ወገኖች የአለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግጋትን እና የጄኔቫ ስምምነቶችን እንዲያከብሩ ጠይቋል። ማኅበሩ አክሎም ሰራተኞቹ እና በጎ ፈቃደኛ አገልጋዮቹ የሌሎችን ህይወት ለመታደግ የራሳቸውን ህይወት በየቀኑ አደጋ ላይ በመጣል የሚሰጡት የሰብአዊ ድጋፍ ያለ ስጋት በገለልተኝነት እንዲያደርሱ ከሁሉም ወገን ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርቧል። ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች በመንግስት የጸጥታ አካላት እና ታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በጉዳዩ ላይ ኃላፊነት የወሰደ ወይም ምላሽ የሰጠ አካል ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ድረስ የለም











