የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገር ውስጥ ባለው የጥቁር ገበያ እጃቸው አለበት የተባሉ አካላት ላይ ሰፊ ክትትል ማድረግ የጀመረ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ እጃቸው አለበት የተባሉ ግለሰቦችን የባንክ ሂሳብ በምስጢር እንዲታገድ ትዕዛዝ አስተላልፎ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
ባንኮች የበርካት ተጠርጣሪዎችን ሂሳብ እንቅስቃሴ እንዲያግዱ፤ የስም ዝርዝር እንደደረሳቸው ምንጮች ለሆርን ፍሪኬዎንሲ ተናግረዋል። ባንኮች የሂሳብ ቁጥር እንዲያግዱ በስም ዝርዝር የደረሳቸውን የጥቁር ገበያ እንቀሳቃሾች መረጃ በጥብቅ ምስጢር እንዲይዙ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።
በዚህም ባንኮች የተሰጣቸው የሂሳብ እንቅስቃሴ የማገድ መመሪያ ወደታች ሳያወርዱ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በኩል እያስፈጸሙ ነው ተብሏል። ብሔራዊ ባንክ ወይም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ይፋ ሳያደርግ ከባንኮች ምንም አይነት መረጃ ሾልኮ እንዳይወጣ የሂሳብ ማገድ እርምጃው በምስጢር እየተከናወነ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
ባንኩ እያደረገ ባለው የጥቁር ገበያ አንቀሳቃሾችን የመቆጣጠር እርምጃ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የተደገፈ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል።
መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት ሐምሌ 2016 ዓ.ም ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ባደረገው ለውጥ የውጭ ምንዛሬ ገበያ መር መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ከፖሊሲ ለውጡ አንድ ዓመት በኋላም የውጭ ምንዛሪው በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ቀጥሏል።
ብሔራዊ ባንክ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የጥቁር ገበያ ለመቆጣጠር ሰፊ ክትትልና እርምጃዎች እየወሰደ ባንኩ ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት እንቅስቃሴ የጥቁር ገበያውን ግስጋሴ ለመግታት በዋና ዋና 138 አንቀሳቃሾች ላይ የባንክ ሂሳብ የማገድ እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል።
ባንኩ እርምጃውን ቀጥሎ ከደላላ እስከ ተቀባይ ድረስ ያለውን የጥቁር ገበያ አንቀሳቃሾችን ሰንሰለት ለመቆጣጠር ሙከራ እያደረገ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል። ብሔራዊ ባንክና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በጥቁር ገበያ አንቀሳቃሾች ላይ ያደረጉትን ሰፊ ክትትል ተከትሎ፣ የበርካታ ተጠርጣሪዎች የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ እየተደረገ ነው።
ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ መግባቱን ተከተሎ፤ ከመደበኛው የባንክ ምንዛሬ እስከ 25 በመቶ ብልጫ አሳይቶ የነበረ የጥቁር ገበያ ግስጋሴ በአንጻራዊነት ረግቧል። ምንም እንኳን በሀገር ቤት በተለይም በአዲስ አበባ ያለው የጥቁር ገበያ ግብት ቢቀዘቅዝም፤ በተለያዩ የውጭ ሀገራት ያለው እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነው።
በየሀገራቱ በተለይም ደግሞ በርከት ያለ ዲያስፖራ በሚኖርባቸው አገራት የጥቁር ገበያው የደራ መሆኑ ይታወቃል። ብሔራዊ ባንክ መሰረታቸው በተለያዩ የውጭ ሀገራት ያደረጉ የጥቁር ገበያ እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር የተለያዩ አማራጮችን እየሞከረ ነው።










