አዲሱን አስተዳደር የተቃወሙ አካላት ጫካ እየገቡ ነው
በህዝባዊ ተቃውሞ ተቀልብሶ የነበረው የአስተዳደር ለውጥ መቀጠሉን ተከትሎ፣ በራያ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን ሆርን ፍሪኩዌንሲ ተረድቷል።
በኃይል የተደገፈው አስተዳደር ለውጥ እንደገና መቀጠሉን ተከትሎ፣ በራያ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ተጠቁሟል። አዲሱን ለውጥ የተቃወሙ አካላትም የአከባቢውን ሚኒሻና ወጣት አስተባብረው ወደ ጫካ እየገቡ ነው ተብሏል።
በህወሓት እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ ተቃውሞ ባሰማው ደቡባዊ ትግራይ ዞን የተሾሙት አዲሱ አስተዳዳሪ ሥራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል። በዚሁ የአስተዳደር ለውጥ እንቅስቃሴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ኃይሎች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት እያስተናገዱ የሚገኙ የራያ አካባቢዎች የባሰ ውጥረት ውስጥ መግባታቸው ተሰምቷል።
እንደ ማይጨውና መሆኒ ባሉ የራያ አካባቢዎች ውጥረት የተፈጠረው፤ በስምምነት እንዲቀር ተደርጎ የነበረው የአስተዳደር ለውጥ መቀጠሉን ተከትሎ ነው። በደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሌተናል ጀነራል ታደሰ ተሸረው፣ ከአንድ ወር ገደማ በፊት የተሾሙት አዲሱ ዋና አስተዳዳሪ ሥራ አቶ ዝናቡ ገብረመድህን ሥራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል። አስተዳዳሪው ከወይን ጋር ባደረጉት ቆይታም ከነሐሴ 20/2017 ጀምሮ አዲስ በተመደቡበት ስፍራ ስራ እንደጀመሩ ይፋ አድርገዋል፡፡
ከጊዜያት አስቀድሞ ጀነራል ታደሰ ወረደ የደቡባዊ ትግራይ ዞን አስተዳደርን ለመለወጥ ሹም ሽር ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በርካታ ተቃውሞዎች ሲሰሙባቸው እንደነበር አይዘነጋም። ይሁን እንጂ የአካባቢው ማኅበረሰብ የተሻሩትን የዞን አስተዳዳሪ ደግፎ ተቃዎሞ በማሰማቱ፣ ጀነራሉ ወደ ማይጨው አቅንተው ውሳኔውን መሻራቸውንም ገልጸው ነበር።
በወቅቱ በኃይል የተደገፈ የአስተዳደር ለውጥ ሲደረግባቸው፤ አልቀበልም ብለው ጫካ ገብተው የነበሩት ሀፍቱ ኪሮስ በስምምነት ወደ ቢሯቸው ተመልሰው ነበር። ምንም እንኳን ሀፍቱ ወደ ቢሯቸው ተመልሰው ዞኑን እያስተዳደሩ ቢሆንም፣ ተቃውሞ የተቀሰቀሰበት የአስተዳደር ለውጥ ዳግሞ እየተፈጸመ መሆኑ ተገልጿል።
የአስተዳደር ለውጡ እየተከናወነ የሚገኘው በራያ አካባቢዎች በተሰማራው የህወሓት ኃይሎችና በጊዜያዊ አስተደደሩ ፖሊስ ነው ተብሏል። አዲሱ የዞን አስተዳዳሪ ሥራ መጀመራቸውን ይፋ ባደረጉበት ዕለት፣ የህወሓት ኃይሎች ወደ ራያ አካባቢዎች በስፋት መግባታቸውን ሆርን ፍርኩዌንሲ ከአካባቢው ምንጮች ሰምቷል።
ከዚህ ቀደም የአስተዳደር ለውጡን ለማስፈጸም ጀነራል ታደሰ፣ በማይጨውና አካባቢው የጸጥታ ኃይል ማሰመራታቸው የሚያስታውሱት ምንጮች፤ በዚህም በራያ አካከቢዎች የአስተዳደር ለውጥ ደጋፊና ተቃዋሚዎች የትግራይ ኃይሎች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት መፈጠሩ ይታወሳል።
እንደ ማይጨው ባሉ የራያ አካባቢዎች የአስተዳደር ለውጡን የሚቃወም ሰልፍ በተደጋጋሚ መደረጉ ይታወሳል። በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ፣ የራያ አካባቢዎችም ክፍፍሉ ውስጥ አንዱን ጎራ የመደገፍ አዝማሚያ እንዳለም ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡










