Home / ፖለቲካ / በአማራ ክልል ተኩስ አቁም እንዲታወጅ ኢሰመጉ ጥሪ አቀረበ

በአማራ ክልል ተኩስ አቁም እንዲታወጅ ኢሰመጉ ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የአማራ ክልል ግጭት ተዋናዮች “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርቧል።

ኢሰመጉ በሰሞነኛ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ የንጹሃንን ተጨማሪ ሞትና ውድመት ለማስቀረት፣ ተኩስ አቁም ታውጆ የግጭቱ ተዋናዮች ወደ ድርድር እንዲገቡ ጠይቋል። የግጭቱ ተዋናዮች መንግሥት እና የፋኖ ኃይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ካወጁ በኋላ፣ ልዩነታቸውን በዘላቂነት ለመፍታት ወይይት እንዲጀምሩ ጉባኤው መክሯል።

ኢሰመጉ መንግሥት እና የፋኖ ኃይሎች ተኩስ አቁም አውጀው ወደ ወይይት እንዲገቡ ጥሪ ያቀረበው፣ በክልሉ በንጹሃን ወገኖች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን በመጥቀስ ነው። የሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች የግጭት አድማስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መቀጠሉን ተከትሎ፣ ግድያን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ጠቅሷል።

ለአብነትም በሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወሰዳ ሳንቃ ጤና ጣቢያ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት፣ በህክምና ላይ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ማረጋገጡን ጉባኤው ገልጿል። በድሮን ጥቃቱ ህይወታቸውን ካጡ ታካሚዎች በተጨማሪ፣ የጤና ጣቢያው የህክምና ባለሙያዎች ተጎድተዋል ብሏል።

በሳንቃ ጤና ጣቢያ ላይ መስከረም 17/2018 ዓ.ም በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በመውለድ ላይ የነበረች ነፍጠሩ እናትን ጨምሮ አራት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ 10 ሰላማዊ ሰዎች በድሮን ጥቃቱ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በክልሉ በደቡብ ወሎ ዞን መካነሰላም ከተማ እና በምዕራብ ጎንደር ዞን በታጣቂዎች በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ከ10 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል።

ተፋላሚ ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ከመፈጸም ተቆጥበው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ኢሰመጉ አሳስቧል።

የፌደራል መንግሥት የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት የማክበር፣ የማስከበርና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጉባኤው ጠይቋል። እንዲሁም የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለማስቆም እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል።

 
 

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *