ከፍተኛ ቅሬታ ተነስቶበታል
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማት ምክንያት አንዳንድ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ እና ከአቅም በላይ የተማሪ ምዝገባ በመፈጸሙ የቦታ ጥበት አጋጥሟል በሚል የመዋዕለ ሕጻናት ተማሪዎች በሳምንት ሁለት እና ሦሰት ቀናት ብቻ እንዲማሩ ተደርገዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ወላጆች ከፍተኛ ቅሬታ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
ቅሬታ አቅራቢ ወላጆች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ እንደገለጹት የፈረቃ አሠራር፡ “በዚህ ሳምንት ሁለት ቀን የተማሩ ተማሪዎች፣ በቀጣዩ ሳምንት ሶስት ቀን እንዲማሩና ሁለቱን ቀናት እረፍት እንዲያደርጉ ይደረጋል” የሚል መሆኑን ነው። ይህ የፈረቃ ትምህርት በተለይ በመንግስት መዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤቶች ላይ እየተተገበረ መሆኑ ተመላክቷል።
በተለይ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ከተጀመረ ገና በቅጡ አንድ ወርም ያልሞላው ቢሆንም፣ ከወዲሁ ሕጉ ከሚያዘው ውጭ ተማሪዎችን በፈረቃ ማስተማር የጀመሩ ትምህርት ቤቶች በርካቶች ናቸው ተብሏል። ለአብነትም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ሰላም በር ቅድመ አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ እንደሆነ ተገልጿል።
በከተማዋ የመንግስት መዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤቶች እየተተገበረ ነው ስለተባለው የፈረቃ የትምህርት ሥርዓት ያውቁ እንደሆነ ብለን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮን አነጋግረናል።
የከተማዋ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ተማሪዎች በፈረቃ እየተማሩ መሆኑን እስካሁን እውቅና እንደሌላቸው ገልጸው፣ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም ትምህርት በፈረቃ እንዲሰጥ ከላይ የተላለፈ ትዕዛዝ እንደሌለ ገልጸው፣ ድርጊቱ ከሕግ ውጭ መሆኑን አስረድተዋል።
በትምህርት ቤቶች በኩል በተደጋጋሚ ከሚነሱባቸው ቅሬታዎች መካከል “ለልዩ ፍላጎት” ተማሪዎች ምቹ አለመሆናቸው እየተገለጸ ባለበት ሁኔታ፣ ትምህርት በፈረቃ መባሉ ትልቅ ችግር ይዞባቸው እንደመጣ ወላጆች ቅሬታቸውን አቅርበዋል።









