Home / ቢዝነስ / የዶላር ዋጋ በምንዛሬ ቢሮዎች እና ጥቁር ገበያ ከፍተኛ ማሻቀብ አሳይቷል

የዶላር ዋጋ በምንዛሬ ቢሮዎች እና ጥቁር ገበያ ከፍተኛ ማሻቀብ አሳይቷል

ብሔራዊ ባንክ ለ10ኛ ጊዜ ለባንኮች በጨረታ ባቀረበው የውጭ ምንዛሬ ላይ የአንድ ዶላር ዋጋ ወደ 148 ብር ማለቱን ተከትሎ፣ የምንዛሬ ቢሮዎችና ጥቁር ገበያ ዋጋ አሻቅቧል፡፡

ከባንኮች በተጨማሪ ከ10ኛው ጨረታ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የመሸጥና መግዛት ፈቃድ የተሰጣቸው የግል የምንዛሪ ቢሮዎች ዋጋቸው ከፍ አድርገዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ዛሬ ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም የመግዛና መሸጫ ዋጋቸው ከፍ አድረገው፣ አንድ ዶላር እሰከ በ165 ብር ድረስ እየገዙ ነው፡፡

ሆርን ፍሪኩዌንሲ ምልከታ ባድርገበት ሮሃ የተሰነው የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮ በዕለቱ አንድ ዶላር በ164 ብር ከ25 ሳንቲም እየገዙ፣ በ167 ብር ከ53 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል፡፡ ብሔራዊ ባንክ አንድ ዶላር በ148 ብር ከማጫረቱ ቀድም ብሎ ይሄው የውጭ ምንዛሪ ቢሮ አንድ ዶላር በ161 ብር ሲገዛ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሌሎች የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎችም በተመሳሳይ የዋጋ ጭማሪ አድርገው አንድ ዶላር እሰከ በ165 ብር ድረስ እየገዙ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎቹ የዶላር አቅርቦታቸው ከባንኮች የተሻለ ዋጋ ስላለው ከፍ ያለ አቅርቦት እንዳላቸው ባደረገነው ማጣራት መረዳት ችልናል፡፡

በሌላ በኩል በአንጻራዊነት መረጋጋት አሳይቶ የነበረው የጥቁር ገበያው የዶላር ምንዛሬ አንሰራርቶ ወደ 170 ተሻግሯል፡፡ ምንም እንኳን በአቅርቦት መጠኑ ልዩነት ያለው ቢሆንም፣ በዛሬው ዕለት አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ እሰከ 172 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለ10ኛ ጊዜ ባካሄደው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ 150 ሚሊየን ዶላሩን 31 ባንኮች የተከፋፈሉ ሲሆን፣ አንድ የአሜሪካን ዶላር ዋጋ በአማካኝ 148.1 ብር ሆኗል፡፡ ባንኩ ባለፈው ጨረታ ለባንኮች ከሸጠበት ዋጋ አንጻር የአንድ ዶላር ዋጋ ከ7 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በዘጠነኛው ዙር ጨረታ ከተመዘገበው የአንድ ዶላር መግዣ 138.2 ብር አማካይ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር፣ የትላንቱ ጨረታ የ9 ብር ከ90 ሳንቲም ወይም የ7.16 በመቶ ጨምሯል። ባንኮች በጨረታ በገዙት የውጭ ምንዛሬ መነሻነት የዋጋ ማሻሻያ ያደረጉ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ በጨረታ ከገዙበት በታች እንደሚሸጡ ያሰራጩት የምንዛሬ ተመን መረጃ ያመላክታል፡፡

ምንም እንኳን ባንኮች የውጭ ምንዛሬ መግዣና መሸጫው በጨረታ ከገዙበት በታች ቢሆንም፣ በሃዋላ ወደ ኢትዮጵያ የሚላክ ዶላር የሚገዙት ከ150 ብር በላይ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ካሽ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋውን በ147 ብር ከ60 ሳንቲም ያደረገው አቢሲኒያ ባንክ፣ ለሃዋላ 9 ብር ጉርሻ ጨምሮ በ156 ብር ከ60 ሳንቱም እየገዛ ነው፡፡

መንግሥት በአበዳሪዎቹ ዓለም ባንክ እና አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) የብድር ቅድመ ሁኔታ፣ የውጭ ምንዛሬ ገበያ መር ካደረገ በኋላ የኢትዮጵያን ብር በከፍተኛ ደረጃ መዳከሙን ቀጥሏል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብር ከዶላር አንጻር ዋጋ ካጡ የአፍሪካ ሀገራት ገንዘቦች ከቀዳሚዎቹ ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *