የጣና ሐይቅ ላይ የቱሪዝም እና የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ በርካታ ወጪ እና ወደ መሃል አገር የማጓጓዝ ስራ የተሰራባት “ጣናነሽ ቁጥር ፪” ጀልባ በአሁኑ ሰዓት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እጀባ ካልተደረገላት ሙሉ አገልግሎት እንደማትሰጥ ተገለጸ።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሻው ለሆርን ፍሪኩዌንሲ እንደገለጹት፣ ጀልባዋ በአሁኑ ሰዓት በሐይቁ ላይ ሥራዎቿን ለመከወን እጀባ ሊደረግላት ይገባል ብለዋል። ኃላፊው እንዳብራሩት፣ ጀልባዋ የቴክኒክ ችግር ገጥሟት ሳይሆን፣ በአካባቢው እየተስተዋለ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በነፃነት መንቀሳቀስ እንድትችል የእጀባ አገልግሎት እስክታገኝ ድረስ በሐይቁ ዳር ቆማ ነው ያለችው። ነገር ግን፣ እስከዚያው ድረስ የጀልባዋን የቀለም መቀባት እና የማስዋብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
አቶ ጋሻው አክለውም ጀልባዋ በአሁኑ ወቅት በሐይቁ ጫፍ ቆማ የምትገኝ መሆኑን ገልጸው፤ የጸጥታው ስጋት ትልቅ ፈተና ሆኗል ብለዋል። ይህ የሚያሳየው ጀልባዋ ሙሉ አቅሟን ተጠቅማ በቱሪዝም እና በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለመስጠት ያላት ፍላጎት፣ በጸጥታው ሁኔታ ፈተና መሆኑን ነው ብለዋል።
ጣናነሽ ቁጥር ፪ ከሌሎች የሐይቁ ጀልባዎች የተሻለች እንደሆነች እና በውስጧም የጥራት ደረጃዋ ከፍተኛ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው ቢገልጹም፣ አገልግሎት መስጠት የምትችለው “የእጀባ አገልግሎት በምታገኝ ሰዓት” ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቢሮ ኃላፊው የጀልባዋን ሙሉ አቅም መጠቀም እንዲቻል የእጀባ ሥራውን ማጠናከር እና የጸጥታው ሁኔታ ላይ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
በጣና ሐይቅ ውስጥ ከዚህ ቀደም በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች ትናንሽ ጀልባዎችን በመጠቀም ከጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው እንደነበር ተነግሯል። እንዲሁም በተለያዩ ወቅቶች ማንነታቸው በውል ያልታወቁ የታጠቁ አካላት በሐይቁ ላይ ጀልባ ተጠቅመው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ንብረት መዝረፋቸውም ተመላክቷል።
በአሁኑ ሰዓት በሐይቁ ዙሪያ የሚገኙ ሌሎች ጀልባዎች ከጣናነሽ ቁጥር ፪ ጋር ተቀራራቢነት ያላቸውን ሥራዎች እያከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። የጎብኚዎች ቁጥር ከፍ ማለት ሲችልና አስፈላጊው የጸጥታ ዋስትና ሲሟላ፣ ጣናነሽ ቁጥር ፪ አገልግሎት መስጠት እንድትጀምር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ንብረት ስትሆን፣ 150 ሜትሪክ ቶን ክብደት እና 38 ሜትር ርዝመት አላት። በተጨማሪም 188 ሰዎችን የመጫን አቅም እንዳላት ተገልጿል።









