በተቀናጀ መንገድ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ አሻጥር ላይ ተሰማርተዋል ያላቸው 112 ተጠርጣሪዎች፣ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልገሎት አስታውቋል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል ሰባት የውጭ አገራት ዜጎች እንደሚገኙበት አገልግሎቱ ያሰረጫው መረጃ ያመላክታል።
ሕገ- ወጥ ሃዋላዎች ፣ የገንዘብ ዝውውሮች፣ የውጭ ምንዛሪ ስወራዎች ፣ የግብር ስወራዎች፣ ሕገ- ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ የማስመሰልና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ እንዲሁም አሸባሪዎችንና የታጠቁ ቡድኖችን ለመደገፍ ሲውሉ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ሕገ ወጥ በሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች፣ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎች፣ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያዎች፣ ሕገ ወጥ የሃዋላ አዘዋዋሪዎችና ደላላዎች፣ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ አሻጥር የፈፀሙ አስመጪዎችና ላኪዎች እንዲሁም ሕጋዊ ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሕገ ወጥ ሃዋላ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ ገንዘብ በማንቀሳቀስ ላይ የነበሩ ናቸው ተብሏል።
በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ አድርገዋል የተባሉ ዓለም አቀፍ የሀዋላ አስተላላፊዎች ፈቃዳቸው ተሰርዟል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው ዓለም አቀፍ የሃዋላ አስተላላፊዎች፣ እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።
እንዲሁም በሀገር ውስጥ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ሀብትን ከሀገር በማሸሽ ላይ ያሉ ድርጅቶች ባለቤቶችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አገልግሎቱ አረጋግጧል።
በተጨማሪም የብሔራዊ ባንክ ሕግን በሚጥስ ሁኔታና ያለምንም ፈቃድ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያን በመጠቀም በሕገ- ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪን ሲያዘዋውሩ የነበሩ አካለት ላይም እርምጃ ተወስዶባቸዋል ተብሏል።
የደህንነት መስሪያ ቤቱ በሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በመከታተል፣ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።










