በጋምቤላ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት የፌዴራል ጸጥታ ኃይሎች ከገቡም በኋላ ቀጥሎ፣ የንፁሃን ሕይወት እየጠፋ ነው።
ግጭቱ መረጋጋቱ በክልሉ መንግሥት ከተነገረ በኋላ ትላንት ታህሳስ 15/2018 ዓ.ም በኢታንግ ልዩ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። በወረዳው በታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ40 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ምንጮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ተናግረዋል።
በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተከፈተው ጥቃት በመቀጠሉ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተጠቁሟል። በግጭቱ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች እየተሳተፉ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሰዎችን በያገኙበት እያጠቁ ነው ተብሏል። በወረዳው ትላንት በተቀሰቀሰው ግጭት ከ100 በላይ ቁስለኞችን ማከሙን ድንበር የለሽ ሐኪሞች የኢትዮጵያ ክንፍ አስታውቋል። በክልሉ በሕክምና ዘርፍ ሰብዓዊ ሥራ ላይ የተሰማራው ተቋሙ፣ ከፍተኛ ቁስለኞችን እያስተናገደ መሆኑን ባወጣው መግጫ ገልጿል።
ተቋሙ በመግለጫው ከአንድ ሳምንት በላይ የዘለቀው ግጭት ተባብሶ መቀጠል የንፁሃን ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ እና ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው ብሏል። የግጭቱ ተባብሶ መቀጠል ባስከተለው አደጋ የጋምቤላ ከተማ ሆስፒታልን ጨምሮ፣ የጤና ተቋማት ቁስለኞችን በማከም ላይ ተጠምደዋል። በጋምቤላ ሆስፒታል መደበኛ የሕክምና አገልግሎት እስከማቋረጥ የደረሰ፣ የቁስለኞች ብዛት እያስተናገደ ነው ተብሏል። በሆስፒታሉ ተመላላሽ ሕክምና የነበራቸው ሰዎች ጭምር አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን።
ሁለት ሳምንት ያስቆጠረው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የክልሉ መንግሥት የሰዓት እላፊ ጥሏል። ጋምቤላ ከተማዋ ጨምሮ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ከምሽቱ ሁለት ስዓት እስከ ንጋቱ 12:00 ድረስ መንቀሳቀስ የከለከለ ሲሆን፣ ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ኃይሎች ውጪ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስም ተከልክሏል።












