የአፍሪቃ ሕብረት እንዲሁም የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችውን የአገርነት እውቅና በይፋ እንደሚቃወሙ እና ውሳኔውንም ውድቅ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
የአፍሪቃ ሕብረት በመግለጫው ሊቀመንበሩ ሞሐሙድ አሊ ዩሱፍ እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችው እውቅና አሳሳቢነቱን ገልጸው ከነጻነት በኋላ የተካለለውን እና በፈረንጆች 1964 በአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ተቀባይነት ያገኘውን ግዛት እንዲከበር እና ሕብረቱም እንደሚጠብቅ አስታውቀዋል፡፡ ሊቀመንበሩ አያይዘውም ሱማሌላንድን እንደ አገር እውቅና ለመስጠት የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እና ሱማሌላንድም የሶማልያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ አካል ሆና እንደምትቀጥል አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ይህ ውሳኔ በቀጠናው ብሎም በአህጉሩ ላይ የሚያስከትለው የጸጥታ ችግር እንዳለ ሆኖ በአፍሪካ ሕብረት ሕግ እና ደንብ ላይም የተቃጣ የደንብ መተላለፍ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ከአፍሪቃ ሕብረት በተጨማሪ የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆም ከእስራኤል በኩል የተሰጠው ሶማሌላንድን እንደ አገር እውቅና የመስጠት ውሳኔን በሚመለከት በዓለም አቀፉ ሕግ መሰረት እስራኤል የሶማልያን የግዛት አንድነት እንድታከበር ያስፈልጋል፤ ሶማሌላንድን እንደ አገር እውቅና መስጠት ደግሞ ይህን የሚጻረር ነው ሲሉም አስታውቀዋል፡፡












