Home / ፖለቲካ / ጅቡቲ በኢትዮጵያ ግዛት የድሮን ጥቃት ፈጸመች

ጅቡቲ በኢትዮጵያ ግዛት የድሮን ጥቃት ፈጸመች

በኢትዮጵያና በጅቡቲ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው በአፋር ክልል ኤሊ ዳኣር ወረዳ፣ የጅቡቲ አየር ኃይል በፈጸመው የድሮን ጥቃት በንጹሃን ዜጎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ገለጹ።

ጥቃቱ የተፈጸመው ዛሬ ጥር 5/2018 ሲሆን በወረዳው ልዩ ስሙ “ሙሁርታ” በተባለ አካባቢ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት በአራት ሰዎች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ማረጋገጣቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ጥቃቱ በተለይ ለከብቶቻቸው ግጦሽና ውሃ ፍለጋ በሚንቀሳቀሱ አርብቶ አደሮች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ድርጊቱ ሆን ተብሎ ማህበረሰቡን ለማሸበር የሚደረግ ስልታዊ ጥቃት ነው ብለዋል። ይህ ጥቃት የተፈጸመው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን አስከትለው በጅቡቲ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ቀን ማግስት መሆኑ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎታል።

በጥቃቱ የቆሰሉ ወገኖችም ተገቢውን የህክምና እርዳታ ባለማግኘታቸው ለከፋ ስቃይ መዳረጋቸውን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው። በኤሊ ዳኣር ወረዳ የጅቡቲ አየር ኃይል የድሮን ጥቃት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው አይደለም ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ልክ ከአንድ ዓመት በፊት በዚሁ ወረዳ “ሲያሩ” በተባለ ቀበሌ ላይ የጅቡቲ መንግስት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት በሁለት ዙር የድሮን ጥቃት ፈጽሞ እንደነበር ተናግረዋል።

በዚያን ወቅት የጅቡቲ መንግስት በወቅቱ የፍሩድ አማጽያንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ነው በማለት ለማስተባበል ቢሞክርም፣ የአሁኑም ሆነ ያለፈው ዓመት ጥቃቶች ሰላማዊ አርብቶ አደሮችን የጎዱ እንጂ ወታደራዊ ኢላማዎችን ያላገናዘቡ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በኤሊ ዳኣር ወረዳ የሚገኙ ንጹሃን በጅቡቲ ድሮኖች ጥቃት እና በኢትዮጵያ መንግስት ዝምታ መካከል ሆነው ለከፍተኛ ስጋት መዳረጋቸውን ተናግረዋል። እስካሁን ባለው መረጃ ከጅቡቲም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግስት ወገን ስለ ድርጊቱ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *