በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ዛሬ ጥር 7/2018 ዓ.ም ካለፈው አራት ዓመት ወዲህ በአማራ ክልል ስር እየተዳደረ በሚገኘው ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ጉብኝት አድርገዋል።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወልቃይትን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከዞኑ አመራሮች ጋሪ መክረዋል። አምባሳደር ማሲንጋ ከዞኑ አመራሮች ጋር መከሩባቸው ዋና ዋና ነጥቦች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ዝግጅት ክፍል ደርሰዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ እና ልዑካቸው ጋር ወደ ሑመራ የተጓዙት አምባሳደሩ፣ ስለ ወልቃይት ታርካዊ እና አሁናዊ ገለጻ ተደርጎላቸዋል። የዞኑ አመራሮች ለአምባሳደሩ በሰጡት ማብራሪያ የወልቃይት ሕዝብ ለተከታታይ ሦስት አስርት ዓመታት፣ ግድያና መፈናቀልን ጨምሮ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፉን አስታውሰዋል።
በወልቃይት ላይ የተነሳው የማንነትና ወሰን ጥያቄ በሕግ አግባብ ከመፍታት ይልቅ በኃይል መታፈኑ፣ ዛሬም ያልተቋጨ ውስብስብ ችግር ማስከተሉንም አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት ወልቃይት በአማራ ክልል ስር እየተዳደረ ቢሆንም፣ የይገባኛል ጥያቄው የመጨረሻ እልባት ባለማግኘቱ የግጭት ስጋት መደቀኑ በውይይቱ ተነስቷል።
በተለይም የፕሪቶሪያው ስምምነት በአግባቡ አለመተግበር አወዛጋቢ ተብለው የተገለጹ የወልቃይት፣ ጠለምትና ራያ ሰላም አለማስፈኑ በውይይቱ ተነስቷል። ስምምነቱ በውል ተፈጻሚ አለመሆኑን ተከትሎ፣ በአወዛጋቢ አካባቢዎች በተለይም በወልቃይት በኩል የዳግም የግጭት መቀስቀስ አደጋ መደቀኑ የውይይቱ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ነበር።
ወልቃይት ላይ የግጭት ስጋት የደቀነው በትግራይ ኃይሎች በኩል ውዝቡን በሕገ አግባብ ከመፍታት ይልቅ፣ ‘ግዛት’ የማስመለስ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባታቸው መሆኑን የዞኑ አመራሮች ለአምባሳደሩ አስረድተዋል። አምባሳደሩ አሁን ላይ ያለውን ሁኔታ እንደሚገነዘቡት የገለጹ ሲሆን፣ የሕዝብን ፍላጎት ከማክበር ውጪ ያሉ አካሄዶች ዘለቂ መፍትሔ እንደማያመልጡ በውይይቱ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ስለ ወልቃይት ጉብኝታቸው በኤምባሲያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ይሄንኑ የሕዝብን ፍላጎት ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
አምባሳደሩት በመልዕክታቸው ሁሉም ወገኖች ከፖለቲካ ይልቅ ሕዝብን እንዲያስቀድሙ እና ሕዝቡ የወደፊት የፖለቲካ ሕይወቱን በትክክለኛው ጊዜ እንዲወስን እድል እንዲሰጠው ጥሪ አቅርበዋል። አምባሳደር ማሲንጋ እያንዳንዱ ዜጋ ደኅንነቱን እና ሰብዓዊ ክብሩን በሚያስጠብቅ ሁኔታ ሕይወቱን የት ቦታ ላይ መመስረት እንዳለበት መወሰን አለበት ብለዋል። ለዚህም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተደገፈ ኢትዮጵያ መር በሆነ የመፍትሔ ሂደት አሜሪካ ትደግፋለች ብለዋል።
አምባሳደሩ ዞኑ አሁን ላይ የሚገኝበትን ሁኔታ ለመገንዘብ በሑመራ ከተማ ተንቀሳቅሰው ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይም የሕክምና እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተዋል። አምባሳደሩ ስለ ሑመራ ጉብኝታቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የተጎዱ መሠረተ ልማቶች፣ የሕክምና እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች እጥረትን ጨምሮ የአካባቢው ሕዝብ ያሉበትን ችግሮች በአካል መመልከታቸውንም ገልጸዋል።












