የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ በኤርትራ ላይ ጦርነት ለመጀመር የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈለገ ነው ሲሉ ለሬውተርስ ተናገሩ።
ከሰሞኑ በአማራ ክልል 56ሺ ተተኳሾች በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ በመንግስት የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ፖሊስ ምንጩ ከኤርትራ መንግስት ሆኖ መዳረሻው ደግሞ ለፋኖ እንደነበር በይፋ ማስታወቁ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ ከኤርትራ ወገን ምላሽ ተሰጥቶበታል። በዚህም ምላሽ “ላለፉት ሁለት ዓመታት የብልጽግና መንግስት በኤርትራ ላይ ሊከፍተው ላሰበው ጦርነት ምክንያታዊ ለማድረግ ሃሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጨ ቆይቷል ” ሲሉ ምለሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የኤርትራ አቻው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቃላት ጦርነታቸው እያየለ መምጣቱን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው መካረር ወደ ቃታ መሳብ ሊያድግ እንደሚችል በርካታ ትንበያዎች ይሰማሉ። በተለይም ደግሞ ከቀናት በፊት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያቸው ጋር ባደረጉት ዘለግ ያለ ቆይታ የኢትዮጵያን መንግስት በግልጽ መዝለፋቸው የታወቀ ሲሆን ይህም ደግሞ መካረሩን የባሰ ወደ ለየለት ደረጃ እንዳይወስደው ተሰግቷል።












