አመልድ ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በመጠለያ ካምፕ ለሚገኙ ወገኖች የሚደረጉ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ዓለም አቀፍ መርሆችን የሚጥሱ ድርጊቶች እየታዩ መሆኑን አስታወቀ።
ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማት እና ከበርካታ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር የሚሰራው፣ አመልድ ኢትዮጵያ በአድሏዊ አሰራሮች ላይ የተሰማሩ አካላት እንዲሁም ሌላ አጀንዳቸውን ለማስረጽ የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡
ተቋሙ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ እየታየ የሚገኘውን ከመርህ ያፈነገጠ ድርጊት፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶች፣ ማኅበራት እና ለጋሽ አካላት እንዲገነዘቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ማንኛውም ድጋፍ ያለምንም የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የባህል እና የዘር ተፅዕኖና አድሉዎ ሊከናወን እንደሚገባ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ አሠጣጥ መርሆዎች እንደሚያስገድዱ ድርጀቱ አስታውሷል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋራ ሥምምነቶች ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ ማንኛውም ግለሰብ የረጂውን አካል እምነት ወይም አስተሳሰብ እንዲቀበል ሳይገደድ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ የማግኘት የማይገሰስ መብት አለውም ብሏል።
የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር፣ እምነትና ሞራል ባልጠበቀ መልኩ፣ ድጋፍን የእምነት ማራመጃና ማስፋፊያ መሣሪያ በማድረግ ተረጂዎችን ለተጽዕኖ የመዳረግ ሁኔታዎች መስተዋላቸው እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አመልድ ገልጿል። ከሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት መርሆች ያፈነገጠ ድርጊቶች በሰብዓዊ ድጋፍ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን መልካም ስም ከማጎድፉም ባለፈ፣ የተረጂዎችን ሞራልና ሰብዓዊ ክብር የሚነኩ መሆኑንም ጠቁሟል።
ድርጅቱ በመግለጫው የተፈነቃይ ወገኖችን ችግር እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የሚፈጸሙ ማናቸውንም በሰብዓዊ ድጋፍ ስም የተረጅዎችን ክብር መንካት፣ እምነት የማስቀየር ጥረትን እና የሞራል ግድፈቶችን በጽኑ አውግዟል፡፡
በአማራ ክልል ያለውን ከፍተኛ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሥራው ላይ የተሰማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሙሉ የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ መርሆዎችን እንዲያከብሩ አሳስቧል፡፡
“ሰብዓዊ አገልግሎት ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው የሚል መርህ ለሁሉም ይሰራል” ያለው አመልድ ኢትዮጵያ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ አሠጣጥ መርሆች እንዲከበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በቅርቡ “አግማስ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ደርጅት ደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ባደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ እና በጎንደር ከተማ ተረጅዎችን ለሃይማኖታዊ ተልዕኮ ለመጠቀም ሙከራ ጋር በተያያዘ ተቃውሞ መነሳቱ ይታወሳል፡፡
በበጎ ሥራዎች ላይ እንደተሰማራ የሚገልጸው ይሄው ተቋም ከማንኛውም የፖለቲካ እና ሃይማኖት ገለልተኛ ነኝ ቢልም፣ ድርጊቱ ውግንናን ያሳያል በሚል ወቀሳ እየደረሰበት ነው፡፡ “አግማስ ኢትዮጵያ” ለተፈናቃዮች ድጋፍ በሚል ባደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ፣ ከባለሀብቱ ወርቁ አይተነው የተለገሰ የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አልቀበልም ማለቱ ይታወሳል፡፡











