Home / ቢዝነስ / በመድሃኒት ላይ የተጣለው ተጨማሪ እሴት ታክስ ታገደ

በመድሃኒት ላይ የተጣለው ተጨማሪ እሴት ታክስ ታገደ

ገንዘብ ሚኒስቴር ያለ ማዘዣ ወይም በጤና ባለሙያዎች ምክር የሚገዙ መድኃኒቶች ላይ የተጣለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ማገዱ ታወቀ፡፡

ማስታገሻዎችን ጨምሮ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚገዙ መድኃኒቶች ላይ መንግሥት ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉ የሚታወስ ሲሆን፤ ከነሐሴ ወር/ 2017 ጀምሮም ግብር ሲሰበሰብባቸው ቆይቷል፡፡ መንግሥት በሐኪም ትዕዛዝ የሚገዙ መድኃኒታችን ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ ቢያደርግም፣ ያለ ማዘዣ በሚገዙ መድኃኒቶች ላይ ተጨማሪ እሴት ግብር እንዲከፈልባቸው ማድረጉ በአተገባበሩ ላይ ውዝግብ ፈጥሯል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ማሳሰቢያን ተከትሎ የፋርማሲ ማኅበራት፣ የመድኃኒት አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ቅሬታ አቅርበዋል። የቀረበውም ቅሬታ መሰረታዊ በሚባሉ እንደ ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ጨጓራ፣ ለጉንፋን፣ የመተንፈሻ አካላት፣ የአንጀት ትላልት የመሰሰሉ በሽታዎች የሚያክሙ መድኃኒቶች ላይ ተጨማሪ ግብር መጣል በማኅበረሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል የሚል ነው። ከማሕበራቱም በተጨማሪ የጤና ሚንስቴርም በመድኃኒት ላይ የተጣለው ተጨማሪ ግብር በማኅበረሰብ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው በመግለጽ ተቃውሞ አሰምቷል።

ቅሬታ የቀረበለት ገንዘብ ሚኒስቴር በመድኃኒት ላይ የተጣለው ተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰብ በጊዜያዊነት እንዲቆም ወስኗል። የግብር አሰባበሰብ አፈጻጸሙም እንዲታገድ መደረጉን ሆርን ፍሩኩዌንሲ ገንዘብ ሚኒስቴር ለገቢዎች ሚኒስቴር ከጻፈው ደብዳቤ ተመልክቷል።

ተጨማሪ እሴት ግብር የተጣለባቸው መድኃኒቶች ከታክስ ነፃ እንዲደረጉ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡም ተጠቁሟል፡፡ የሕግ ማሻሻያው እስኪጸድቅ ድረስ ገቢዎች ሚኒስቴር በባለሙያዎች ወይም ያለ ማዘዣ ወረቀት የሚገዙ መድኃኒቶች ላይ ተጨማሪ ግብር መሰብሰብ እንዲያቆም ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *