ከአንድ ዓመት በፊት ባጋጠመው የጎፋ መሬት መንሸራተት ለተጎጂዎች ከተሰበሰበው የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ 60 ሚሊዮን ብር ለመመዝበር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ባለሥልናት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡
ከ200 በላይ ሰዎች ህወይታቸውን ላጠቡት አደጋ የተሰበሰበውን ገንዘብ ለመመዝበር የባንክ ቼክ አዘጋጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት መያዛቸውን ዞኑ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች ከተሰበሰበው እርዳታ 60 ሚሊዮን ብር ለመመዝበር የሞከሩት የቼክ ቁጥር አሰመስለው በማሳተም ነው ተብሏል፡፡ ተመሳስሎ በተዘጋጀው ቼክ ወጪ የተጠየቀው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለጎፋ ዞን አስተዳደር በተደረገ ጥቆማ መስጠቱን ተከትሎ፣ በፖሊስ ክትትል ገንዘቡ ሳይወጣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተገልጿል።
ምንም እንኳን ለመሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጅዎች የተሰበሰበሰው ገንዘብ ለመመዝበር ሙከራ ያደረጉት አካላት በውል ባይገለጽም፣ ባለሥልጣናት እንደሚገኙበት ተሰምቷል፡፡ በጉዳዩ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ባለሥልጣናት መካከል የዞኑ ፋይናንስ እና አደጋ ሥጋት መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ200 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። በአደጋው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ገንዘብ መሰብሰቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ተጎጅዎችን ከማቋቋም አንጻር ቅሬታ ሲነሳ ነበር፡፡









