በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማት የተሰሩ የንግድ ቤቶች ኪራይ ጨረታን ለማሸነፍ በሚልዮኖች ብር ጉቦ እየተጠየቀበት መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሱት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በመዲናዋ በተለያዩ አደባባዮችና መንገድ ዳር በኮሪደር ልማት የተገነቡ የመንግሥት የንግድ ቤቶች በሁለት ዙር ለጨረታ ቀርበው ነበር። ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር የበላይነት የሚመራው የኮሪደር ንግድ ቤቶች ጨረታ ለከፍተኛ ጉቦ መጋለጡን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሆርን ፎሪኩዌንሲ ተናግረዋል።
የኪራይ የጨረታ ውድድር ውጤቱን አስቀድመው የሚወስኑ በጥቅም የተያያዙ የቤቶች ልማትና አስተዳደር የጨረታ አስፈጻሚ አመራሮች ናቸው ተብሏል። በዚሁ የተነሳ በጨረታው የተሳተፉ ነጋዴዎች የኪራይ ቤቶቹን በነጻ ገበያ ውድድር ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸውልናል።
ለጨረታ የሚቀርቡ የንግድ ሱቆችን የኪራይ ውድድር ለማሸነፍ፣ ነጋዴዎች እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር እንደሚከፍሉ ዝግጅት ክፍላችን ባደረገው ክትትል ተረድቷል። በቅርቡ ወጥቶ በነበረው የሁለተኛ ዙር የኮሪደር ንግድ ሱቆች የኪራይ ጨረታ ላይ አንድ ነጋዴና የቢሮው ሰራተኞች፣ በሦስተኛ ወገን ደላላ ያደረጉትን ምልልስ ተከታትለናል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው የማይገለጽ አንድ ነጋዴ መገናኛ አካባቢ የሚገኝ በኮሪደር ልማት የተገነባ የንግድ ሱቅ ኪራይ ጨረታ ለማሸነፍ፣ የአንድ ሚሊዮን ብር ጉቦ ለቤቶች ልማትና አስተዳደር የጨረታ አስፈጻሚ አመራሮች ማቅረባቸውን ለማረጋገጥ ችለናል። ይሁን እንጂ በጨረታ አስፈጻሚው የቤትና ልማት ሰዎች በኩል ለእጅ መንሻ የቀረበው አንድ ሚሊዮን ብር በቂ እንዳልሆነ እና ጨረታውንም ለማሸነፍ እንደማያበቃቸው በመገለጹ መስማማት ላይ ሳይደርሱ መቅረታቸውንም ዝግጅት ክፍላችን ባደረገው ማጣራት ለማረጋገጥ ተችሏል።
የጨረታ አሰራሩ በደላሎች እጅ ገብቶ ለብለሹ አሰራር መጋለጡን የተረዱ ነጋዴዎች፣ በሂደቱ ላይ ለቤቶች ልማትና አሰተዳደር ቢሮ ቅሬታ አቅርበዋል። በዚህም መሰረት ቢሮው ከተጫራቾች የቀረቡለትን ቅሬታዎች ተቀብሎ እንደሚመረምር የገለጸ ቢሆንም፣ አሰራሩ ግልጽ እንደነበር ከመግለጽ የዘለለ የሰጠው ምላሽ እንደሌለ ምንጮች ገልጸዋል። ቢሮው በጨረታ ሂደቱ ላይ የቀረበለትን ቅሬታ መርምሮ አገኘሁት ያለውን ውጤት፣ ቅሬታ አቅራቢ ተጫራቾች በአካል ቀርበው እንዲመለከቱ አድርጓል።
ይሁን እንጂ ቢሮው ለቅሬታ አቅራቢዎች የሰጠው ምላሽ፣ በውጤቱ ላይ ምንም አይነት ለውጥ የማያመጣ ነው ተብሏል። በዚህም መሰረት ህጋዊ መንገድ ተከትለው በጨረታው ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች አሸናፊ የሚሆኑበት እድል በዕጅጉ የጠበበ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡









