Home / ቢዝነስ / በትግራይ ክልል የጥሬ ገንዘብ እጥረት ተከስቷል

በትግራይ ክልል የጥሬ ገንዘብ እጥረት ተከስቷል

በድንበር አካባቢ የኤርትራ ገንዘብ ናቅፋ ግልጋሎት ላይ እየዋለ ነው

የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ በተለይም በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አቅራቢ በሚገኙ ከተሞች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው ተብሏል። እንደ አዲግራት፣ አክሱም፣ አድዋና ሽሬ ባሉ ከተሞች ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚሰጡት ጥሬ ገንዘብ ውስን መሆኑን እና ተጠቃሚዎች በሚፈልጉት መጠን እንዲሁም በአሻቸው ጊዜ ገንዘባቸውን ከባንክ ወጪ ማድረግ እንደማይችሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አንድ የአዲግራት ከተማ ነዋሪ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጥሬ ገንዘብ ወጪ ጠይቀው፣ የለም እንደተባሉ እና ይህም ደግሞ በእርሳቸው ብቻ ሳይሆን በርካታ የባንክ ተጠቃሚዎችም የሚያጋጥማቸው ምላሽ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ከኢትዮ-ኤርትራ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው አዲግራት ከተማ የጥሬ ገንዘብ እጥረት የተከሰተው፣ ከሁለት ሳምንት ገደማ ወዲህ መሆኑ ተጠቁሟል። በዚህ ከተማ በአንድ ጊዜ ሦስት ሺ ብር ያህል ማውጣት እንኳን እንደማይቻል ለማወቅ ተችሏል፡፡

የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌ ጭምር የሚስተዋል ቢሆንም፣ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ከተሞች ላይ የባሰ ነው ተብሏል። የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ ምክንያት ከዳግም ጦርነት መቀስቀስ ስጋት እና የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት መሆኑ ተጠቁሟል። በትግራይ ክልል ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚለው ስጋት፣ ነዋሪዎች የምግብ ፍጆታዎችን በብዛት ለመሸመት አስገድዷቸዋል።

የክልሉ ነዋሪነት የፍጆታ ሸመታ ፍላጎት ከፍ ማለትና ጥሬ ገንዘብ በመያዝ እንቅስቃሴ በስፋት እየታየ ነው ተብሏል። ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚለው ስጋት የኑር ውድነትን ማባባሱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባሰራጨው መረጃ አረጋግጧል። ለጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት የሆነው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ኮንትሮባንድ ንግድ ማጧጧፉን ምንጮች ገልጸዋል። የኮንትሮባንድ ንግዱ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር፣ የኤርትራ ናቅፋ ወደ ገበያ እንዲገባ በር መክፈቱ ተሰምቷል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በኢትዮ ኤርትራ ድንበር አካባቢ አንዳንድ ስፍራዎች ላይ የኤርትራ ናቅፋ ከብር ጎን ለጎን መገበያያ መሆኑን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

የኤርትራ ገንዘብ ናፍቃ ወደ ኢትዮጵያ ትግራይ ገብቶ በተለይ በድንበር አቅራቢ ከተሞች በስፋት እየተሰራጨ መሆኑ ደግሞ ማሳያው ከሰሞኑ ከኤርትራ ወደ ራማ ድንበር በኩል የገባ ግማሽ ሚሊዮን ገደማ ናፍቃ ወደ ማኸል ትግራይ ሲገባ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምተናል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዝግጅት ክፍላችን በክልሉ ያጋጠመውን የገንዘብ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት ከብሔራዊ ባንክ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ የብሔራዊ ባንክ የስራ ኃላፊዎች ከዝግጅት ክፍላችን ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጡን ቀርተዋል፡፡

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *