Home / ማህበራዊ / ‹‹ለአገር ውስጥ ሚዲያዎች ጥሪ ብናደርግም የተገኘ ሚዲያ አልነበረም›› የአክሱም ከተማ ቱሪዝም ቢሮ

‹‹ለአገር ውስጥ ሚዲያዎች ጥሪ ብናደርግም የተገኘ ሚዲያ አልነበረም›› የአክሱም ከተማ ቱሪዝም ቢሮ

በየዓመቱ በታላቅ ኃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓትና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ተሳትፎ በድምቀት የሚከበረው የቅድስት ማርያም አክሱም ጽዮን ክብረ በዓል፣ ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ሽፋን ሙሉ በሙሉ እንዳልሰጡት የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አስታወቀ።

ቢሮው እንዳስታወቀው ከዚህ ቀደም ለበዓሉ ትልቅ ቦታ ይሰጡ የነበሩ የመንግስት ሚዲያዎችን ጨምሮ ሌሎች የግል የዜና ማሰራጫዎች በሙሉ ጥሪ ቢደረግላቸውም ሳይገኙ ቀርተዋል ሲል ጨምሮ ገልጿል።

ሚዲያዎቹ ይህን ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ለመዘገብ ሳይገኙ የቀሩበት ዋና ምክንያት በክልሉ በትግራይ ውስጥ ያለው አሁናዊ ውጥረትና አለመረጋጋት ሊሆን እንደሚችል አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት በክልሉ ውስጥ የቅርንጫፍ ቢሮ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡

የአክሱም ጽዮን ማርያም በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ ከዓመቱ ታላላቅ ክብረ በዓላት አንዱ ነው። የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች በቦታው አለመገኘት፣ በዓሉ በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን በተመለከተ ለብዙኃኑ ምዕመናን ሊደርስ የሚገባው ተጨባጭ መረጃ ሳይደርስ ቀርቷል፤ ይህም ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት ፈጥሯል ሲል የክብረ በዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አስታውቋል።

ክስተቱ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለው ሁኔታ በሲቪልና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ጭምር ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ ይህ ኃይማኖታዊ በዓልም ለዓለም አቀፍ ተመልካቾች በተለመደው የጥራት ደረጃ ሳይተላልፍ ቀርቷል ሲሉም አክለዋል።

ይሁን እንጂ የዝግጅት ክፍላችን በታዘበው መሰረት ከመላው የኢትዮጵያ ክፍል ዓመታዊ በዓሉን ለማክበር ወደ ታሪካዊቷ አክሱም ከተማ በርካታ ምዕመናን ተጉዘዋል፡፡

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *