Home / ቢዝነስ / ወልቃይት የተፈጠረው ምንድነው?

ወልቃይት የተፈጠረው ምንድነው?

ባለፉት ጥቂት ቀናት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በወርቅ ማውጣት ሥራ ላይ በተሰማሩ ወጣቶች እና በአካባቢው አስተዳደር መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ሰንብቷል። ይህንኑ ተከትሎ በተከሰተ ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱና በመጨረሻም ጉዳዩ በውይይት መፈታቱ ታውቋል።

ለግጭቱ መነሻ የሆነው የዞኑ አስተዳደር በቃፍታ ሑመራ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የሚካሄደውን የወርቅ ፍለጋ ሥራ ለማገድ ያስተላለፈው አዲስ ውሳኔ ነው። አስተዳደሩ ውሳኔውን ያስተላለፈው በፓርኩ ውስጥ የሚከናወነው የወርቅ ማውጣት እንቅስቃሴ የዱር እንስሳትን እያሰደደና ብሔራዊ ፓርኩን ለከፍተኛ ውድመት እየዳረገ ነው በሚል ምክንያት ነበር። በዚህም ወጣቶቹ ከፓርኩ ክልል ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላለፈ። ይህንን ትዕዛዝ ያልተቀበሉ ወጣቶች፣ ውሳኔው የሥራ ዕድላችንን ይዘጋል በሚል ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ ዞኑ መቀመጫ ሑመራ ከተማ በማቅናት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ሆኖም ሰልፉ ወደ ግጭት በማምራቱ ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ጉዳዩ የማይመለከታቸው እና በአካባቢው በመንቀሳቀስ ላይ የነበሩ ሁለት ወጣቶች ሕይወታቸው አልፏል።

በወቅቱ በተፈጠረው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ላይም የመቁሰል አደጋ ደርሷል። የሁኔታውን መባባስ ተከትሎ የዞኑ አስተዳደር ውሳኔውን የሻረ ሲሆን፣ ከወጣቶቹ ጋርም ሰፊ ውይይት አድርጓል። በተደረገው ስምምነት መሠረት ወጣቶቹ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የተፈቀደ ቢሆንም፣ ሥራው ግን የዱር እንስሳትን በማይረብሽ እና የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር በማይጎዳ መልኩ እንዲከናወን ጥብቅ አቅጣጫ ተቀምጧል። በአሁኑ ወቅት ሕይወታቸውን ያጡት ወጣቶች የቀብር ሥነ-ሥርዓት የተፈጸመ ሲሆን፣ በከተማዋ ተፈጥሮ የነበረው ውጥረት ረግቦ ወጣቶቹ ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።

ሆርን ፍሪኩዮንሲ ስለ ሁኔታው ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለውን በተደጋጋሚ ለማነጋገር ቢሞክርም፣ ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *