በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን በሱሪ ወረዳ በጉብኝት ላይ እያሉ፣ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት የቱርክ ዜጎች እና አንድ ኢትዮጵያዊ መገደላቸውን ክልሉ አስታውቋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ዛሬ ጥር 4/2018 ከጥዋቱ 2 ሰዓት ከ20 ላይ ሰዎች በጉብኝት ላይ ባሉበት አጋጣሚ ነው ተብሏል። የጥቃቱ ፈጻሚዎች ‘ሽፍቶች’ መሆናቸውን ክልሉ የገለጸ ሲሆን፣ ሁለቱ የቱርክ ዜግነት ያላቸው ጎቢኚዎች ሲሆኑ ኢትዮጵያዊው ደግሞ አሽከርካሪ እንደነበር ታውቋል።
ክልሉ ለዝርፊያ ዓላማ ጥቃት ፈጽመዋል ያላቸው አካላት ማንነታቸው የማይታወቅ “የአርብቶ አደር ሽፍቶች” በማለት ገልጿቸዋል።
ጥቃቱን ፈጽመዋል በተባሉ ‘ሽፍቶች’ ላይ የተቀናጀ የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጀመሩን ክልሉ ጠቁሞ የክልሉ መንግሥት ግድያ የፈጸሙትን ‘ሽፍቶች’ ተከታትሎ፣ ለሕግ ለማቅረብ የተቀናጀ የጸጥታ ኃይል ማሰማራቱን አስታውቋል።
የክልሉ መንግሥት የህግ የበላይነት ለማስከበር በሚያደርገዉ ጥረት የአካባቢው ማኅበረሰብ የጥቃት ፈጻሚዎቹን ማንነት በማጋለጥ ለፀጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።











