Home / ፖለቲካ / የአዲስ አበባ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

የአዲስ አበባ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው ሀገራዊ ምክክር፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ምንጮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ተናግረዋል።

አንድ ወር የዘለቀው የምክክር ጉባኤ በመጨረሻው ምዕራፍ አጣብቂኝ ውሰጥ የገባው፣ የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች “አቋማችን ምክረ ሀሳብ ሆኖ ካልጸደቀ አመጽ ይቀሰቀሳል” በማለታቸው ነው ተብሏል። የክልሉ ተወካዮች “አዲስ አበባ የኦሮሚያ መቀመጫ መሆኗ በሕገ መንግሥት ይረጋገጥ” የሚለው አቋማቸው አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በተመካካሪዎችና በኮሚሽኑ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።

በምክክር ጉባኤው አዲስ አበባ ራሷን በራሷ የምታስተዳድር ተጠሪነቷ ለፌደራሉ መንግስት የሆነች ከተማ ትሁን የሚለው ምክረ ሀሳብ ያለ ተጨማሪ አማራጭ ስምምነት ላይ ተደርሶበታል ተብሏል። ስምምነቱ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም ለ4 ሺህ የምክክር ጉባኤው ተመካካሪዎች ቀርቦ ሊጸቅ የነበረ ቢሆንም፣ ከኦሮሚያ ተወካዮች በኩል “ግጭት ይቀሰቀሳል” በሚል በተፈጠረው ጫና ሳይጸድቅ ቀርቷል።

ጉባኤው የተስማማባቸውን የስምንቱም አጀንዳ ምክረ ሀሳቦች፣ ለማጽደቅ ከተሰበሰበ በኋላ ተበትኗል። የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች በአዲስ አበባ ጉዳይ አቋማችን ካልተከበረ፣ የጉባኤውን ውሳኔም እንደማይቀበሉት በኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በኩል ተናግረዋል።

የክልሉ ተወካዮች ለብቻቸው ከኮሚሽነሮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ይቀሰቀሳል ያሉትን ግጭት አረጋግተው መያዛቸውን በመግለፅ ጭምር አስጠንቅቀዋል ተብሏል። ተወካዮች ጨምረውም የአዲስ አበባ ጉዳይ እልባት የማያገኝ ከሆነ ሊመጣ ያለው ግጭት ከፍተኛ መሆኑን እና ከእነርሱም አቅም በላይ መሆኑን አስታውቀዋል::
በዚህም ምክንያት ኮሚሽኑ በምክክር ጉባኤው አብዛኛው ተመካካሪ የተስማማበትን ምክረ ሀሳብ፣ እንደገና እንዲከልስ ከተቀመጠው አስራር ስርዓት ውጭ አስማሚ ኮሚቴ አደራጅቷል።

ጉዳዩን 320 አባላት ያሉት የክልል ጉባኤ እንዲመለከተው የተሞከረ ቢሆንም፣ ስምምነት ላይ አልተደረሰበትም። የክልል ፕሬዝዳንቶችና የሁለቱ የፌደራል ከተሞች ከንቲባዎች በተገኙበት በተደረገው ስብሰባ፣ የማይታረቁ ሀሰቦች ቀርበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ አዲስ አበባ የክልሉ መቀመጫ መሆኗ ላይ አንደራደርም ማለታቸውን ምንጮች ገልጸዋል። ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት፣ ከተማዋ “በኦሮሚያ ግብዓት ስለተገነባችና በክልሉ መሃል ስለምትገኝ” የሚል መሆኑ ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አረጋ ከበደ፣ አዲስ አበባ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀብት የተገነባች የጋራ ሀብት ነች የሚል ሀሰብ አንስተዋል ተብሏል። ምንም እንኳን አብዛኛው ተማካካሪ የተስማማ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ከመግባት አጀንዳው በይደር ይቆይ የሚል ሀሳብ አቅርበዋል ተብሏል።

ይሁን እንጂ በኦሮሚያ ተወካዮች በኩል የተያዘው አቋም፣ የአብዛኛው ተመካካሪ ምክረ ሀሳብም እንዳይጸድቅ፣ አጀንዳውም እንዳያድር የማድረግ አካሄድ ነው ተብሏል። አዲስ አበባ የኦሮሚያ መቀመጫ መሆኗ በሕገ መንግሥት ካልተረጋገጠ፣ የምንስማማበት ጉዳይ የለም በማለት ኮሚሽኑን ጭምር ጫና ውስጥ ማስገባታቸው ተጠቁሟል።

በዚህም ኮሚሽኑ የተጠናቀቀው የምክክር ጉባኤ፣ የመጨረሻ ስምምነት ለማስፈጸም ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ምንጮች ገልጸዋል። በተፈጠረው አጣብቂኝ አጠቃላይ የምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች፣ የመረበሽ ስሜት ውስጥ መግባታቸው ተመላክቷል።

Tagged:

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *