የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ላለፉት ስድስት ወራት የአገር ውስጥ የዘገባ ፈቃዱ እንዳይታደስ ከልክሎት የነበረውን የዓለም አቀፉ የዜና አውታር ሬውተርስን ፈቃድ ማደሱን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከዜና አውታሩ የበላይ አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ ከመከረ በኋላ ፈቃዱን ማደሱን ጨምሮ አስታወቋል። የሬውተርስ ሶስት የኢትዮጵያ ቋሚ ዘጋቢዎች ፈቃድ የታደሰው ከዚህ ቀደም ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ የዜና አውታሩ ያሳራጫቸው ዘገባዎች የአገርን ጥቅም እና የሚዲያ ህጉን የሚጻረሩ ነበሩ በሚል ከሬውተርስ ኤክስክዩቲቭ ኤዲተር ኒክ ታተር እና የአፍሪካ ኤዲተር ሲልቪያ አሎይሲ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው። የተቋሙ የኢትዮጵያ ቋሚ ዘጋቢዎች ፈቃድ አለመታደስን ተከትሎ በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚሰሩ ዘገባዎች ባለፉት ስድስት ወራት ከኬንያ ናይሮቢ በሚገኘው የዜና ክፍል ይጠናቀሩ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሬውተርስን ጨምሮ የዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ፈቃዳቸው እየተሰረዘ በጋዜጠኞች እና በሚዲያ ተቋማት ላይ ከፈተኛ እንግልት እና ዝርፊያ ሲካሄድ እንደነበር ይታወቃል። ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት በይፋ እግድ ከተጣለባቸው የሚዲያ ተቋማት ውስጥ በይፋ እግዱ የተነሳለት እና ለዘጋቢዎቹ ፈቃድ የታደሰለት የሚዲያ ተቋም ሬውተርስ ብቻ ነው።
ከባለስልጣኑ ጋር የተወያዩት የሬውተርስ የስራ ኃላፊዎች ወደፊት ስህተት ናቸው የተባሉ ጉዳዮች እንዳይደገሙ እና እንዳያጋጥሙ ጠንካራ የኢዲቶሪያል ክትትል እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።












