Home / ማህበራዊ / በቤንሻንጉል ክልል መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደረጉ

በቤንሻንጉል ክልል መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደረጉ

ከፌደራል መንግሥት የተመደበለት የተጨማሪ ደመወዝ በጀት በቂ አይደለም ባለው፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መምህራን የሥራ ማቆም አድማ መጀመራቸውን ተገልጿል።

በመተከልና ካማሺ ዞኖች ከትናንት ህዳር 1/2018 ዓ.ም መምህራን የሥራ ማቆም አድማ መምታታቸውን የአካባቢው ምንጮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አስታውቀዋል፡፡

ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ ይተገበራል የተባለው የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ መዘግየት የሥራ ማቆም አድማ ከመምህራን በተጨማሪ በሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ዘንድም እየተስተዋለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመስከረም ወር ሲጠበቀ የነበረው የደመወዝ ጭማሪ በተጠናቀቀው ጥቅምት ወርም አለመከፈሉን ተከትሎ፣ መንግሥት ሠራተኛው ተቃውሞ እያሰማ መሆኑ የዝግጅት ክፍላችን ካሰባሰበው መረጃ ተረድቷል።

በመተከል ዞን ውስጥ ብቻ ከ20 በላይ ትምህርት ቤቶች በመምህራን የሥራ ማቆም አድማ ትምህርት ተቋርጧል ተብሏል። በተመሳሳይ በካማሺ ዞን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች መምህራን የሥራ ማቆም አድማ መምታታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግሥት የፌደራል መንግሥት የመደበለት የደመወዝ ጭማሪ፣ ለሁሉም የክልሉ የመንግስት ሠራተኛ ለመክፈል እንደማይበቃው በመግለጽ ውሳኔው አስተላልፏል። ክልሉ የገጠመው የበጀት ጉድለት የ1.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከመስከረም ጀምር የ10 ወር የተጨማሪ ደመወዝ በጀት ተለቆለታል።

ከመስከረም ወር ጀምሮ ይከፈላል ተብሎ በጥቅምት ወርም የቀረው የደመወዝ ጭማሪ፣ በተለያዩ ክልሎች በሠራተኛው ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል። ክልሎች የደመወዝ ጭማሪውን በበጀት ጉድለትና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መዘግየት በወቅቱ መክፈል አለመቻላቸውን በመግለጽ፣ ያለፉትን ሁለት ወራት ጨምሮ በህዳር ወር እንደሚከፍሉ በመግለጽ ሠራተኛውን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ ነው።

አዲሱን የደመወዝ ጭማሪ ከሁሉም ቀድሞ የተከፈለው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች መሆኑን ዝግጅት ክፍላችን አረጋግጧል። በከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች የመስከረም ወር ተጨማሪ ደመወዝ ጥቅምት አጋማሽ የተከፈላቸው ሲሆን፣ የጥቅምት ወር በተሻሻለው ደመወዝ ስኬት ተከፍሏቸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *