ፖሊስ ጉዳዩን አስተባብሏል
በየዓመቱ በወርሐ ነሐሴ በአማራ እና በትግራይ ማህበረሰብ በዋናነት በልጃገረዶች በልዩ ድምቀት የሚከበሩት የሻደይ፣ አሽንዳ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት ዝግጅቶች በአዲስ አበባ እንዳይከበሩ መከልከላቸው እና የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች በፖሊስ መበተናቸው ሆርን ፍሪኩዌንሲ አረጋገጧል፡፡
በመጀመሪያ ለሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል ክብረ በዓል በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ ባለ አንድ መዝናኛ ስፍራ ዝግጅት ተሰናድቶ የነበረ ቢሆንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት በሆኑ የጸጥታ አካላት ዝግጅቱ መከልከሉን እና ታደሚዎችም ወደ ስፍራው እንዳይገቡ መታገዳቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ከስፍራው ዝግጅቱን የተከለከሉ ስዎች ሌላ ዝግጅት ይደረግበት ወደነበረው የኔክሰስ ሆቴል አቅንተው ነበር፡፡ በዚህም ሆቴል ውስጥ የጸጥታ አካላት በመገኘት ዝግጅቱ እንዳይካሄድ ከልክለዋል፡፡ አዘጋጆችም ለጥቂት ሰዓታት በፖሊሰ ቁጥጥር ስር ውስጥ ገብተው እንደነበር የዝግጅት ክፍላችን የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ የአሸንዳ በዓልን ለማክበር ዝግጅት ሁሉ ተጠናቆ እና በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ አንድ የመዝናኛ ስፍራ ታቅዶ የነበረው ዝግጅት ትኬቶች ተሽጠው ካለቁ እና ለዝግጅቱም ሰዓታት ሲቀሩት አዘጋጆች በውል ባልጠቀሱት ነገር ግን ባልተጠበቀ ምክንያት በሚል ዝግጅቱ ላለተወሰነ ጊዜ እንዲተላለፍ መወሰኑን የሚገልጽ መልዕክት አሰራጭተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሆርን ፍሪኩዌንሲ በጉዳዩ ላይ ባደርገው ማጣራት ከመንግስት የጸጥታ አካላት ክልከላው እንደደረሳቸው ተረጋግጧል፡፡
በተፈጠረው ክልከላ በግንባር ቀደምነት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ቢታዩም የብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት ባልደረቦችም በስፍራው በተሽከርካሪ ውስጥ ሆነው ይታዩ እንደነበር ታውቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለሆርን ፍሪኩዌንሲ በሰጠው ምላሽ የተባለው ክልከላ ያልተፈጠረ እና ሐሰት ነው ሲል አስታውቋል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ በምላሻቸው እንዳስወቁት ይህ ባህልን የማስተዋወቅ ዝግጅት ነው ፖሊስ ምንም አያገባውም ሲሉም አክለዋል፡፡










