በዩንቨርስቲዎች ስለ ለሚያስተምሩ መምህራን የተባለ ነገር የለም
በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ትምርህታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች በክልሉ ካለው ነባራዊ የሰላም እጦት ችግር ጋር በተያያዘ ባቀረቡት ቅሬታ መሰረት በሌሎች የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በጊዜያዊነት እንዲመደቡ መደረጉን ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ።
በትግራይ ክልል በተፈጠረው የጦርነት ዳግም መቀስቀስ ስጋት፣ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎችቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ከትምህርት ሚነስቴር ሚንስትር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸውም በአሁኑ የትምህርት ዘመን ከነበሩባቸው በትግራይ ክልል ከሚገኙ ዩንቨርስቲዎች ውጪ በጊዜያዊነት በሌሎች አካባቢዎች ዪንቨርስቲዎች እንደሚመደቡ መወሰኑ እና ትኩረታቸው ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲሆን ሚንስትሩ መናገራቸው ታወቋል።
በክልሉ አስቻይ ሁኔታ እስኪፈጠር በሌሎች የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በጊዚያዊነት እንዲመደቡ የተደረጉት ተማሪዎች ለምዝገባ በአካል ወደ ትምህርት ሚኒስቴር መምጣት ሳይጠበቅባቸው ይፋ በሚደገው የበየነ መረብ አማራጭ በመጠቀምመመዝገብ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
ሚንስቴሩ ይህን ውሳኔ ያሳልፍ እንጂ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩንቨርስቲዎች የሚያስተምሩ መምህራን እጣ ፈንታቸውን በሚመለከት ምንም የተላለፈ ውሳኔ አለመኖሩ ታውቋል። ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አስተያየታቸውን የሰጡ የዩንቨርስቲ መምህራን እንደሚናገሩት ውሳኔውን በመገናኛ ብዙኃን ከመስማታቸው በፊት ምንም የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል በሕወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል እየተካረረ የመጣውን ችግር እንዲሁም የክልሉ መንግስት በግልጽ እንደተናገረው ግልጽ ጦርነት ታውጆብኛል ከማለቱ ጋር ተያይዞ በርካታ የድሮን ድብደባዎች መረጃዎች ጎን ለጎን እየወጡ ይገኛሉ። በዚህም መሰረት በቀጣይ ከፍ ወዳለ የጦርነት ደረጃ እንደሚገባ ይጠበቃል። የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ከርዕዮት ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከሕወሓት በኩል የአጸፋ ምላሽ ካለመስጠት ባሻገር የፌደራል መንግስት ግልጽ እና ይፋዊ ጦርነት በትግራይ ላይ ከፍቷል ሲሉ ተደምጠዋል።











