ባለፈው ሕዳር ወር ላይ በጎንደር ከተማ አቅራቢያ ልዩ ስፍራው ማክሰኚት በተባለ አካባቢ በታጠቁ ኃይሎች ታግቶ የነበረው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የጎንደር ቅርንጫፍ ባልደረባ፣ አጋቾቹ የጠየቁት የ300 ሺህ ብር ክፍያ ተፈጽሞ መለቀቁን ዝግጅት ክፍላችን አረጋግጧል።
ጋዜጠኛ ደስታ ካሳ ለስራ ጉዳይ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ከጎንደር በመነሳት ወደ ባህር ዳር በመጓዝ ላይ እያለ፣ ከጎንደር ከተማ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው ማክሰኚት ከተማ አቅራቢያ ታጣቂዎች የሕዝብ ማመላለሻ መኪናውን አስቁመው በመፈተሽ እሱን እና ሌሎች ተሳፋሪዎችን ይዘው ወደ ጫካ ወስደዋቸው የነበረው።
የጋዜጠኛው መታገት እንደተሰማ ቤተሰቦቹና የቅርብ ወዳጆቹ ከፍተኛ ስቃይና ጭንቀት ውስጥ የቆዩ ሲሆን፤ ጋዜጠኛውን ለማስለቀቅ የተጠየቀውን የገንዘብ መጠን ለማሟላት በርካታ ርብርብ አድርገው በስተመጨረሻም ጋዜጠኛውን ማስለቀቅ እንደተቻለ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡
ይህ የጋዜጠኛው እገታ በብቸኝነት የሚታይ ክስተት ሳይሆን በአካባቢው በየቀኑ እየተፈጸመ ያለ ሰቆቃ ማሳያ ነው ሲሉ ሰለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በጎንደር እና ባህር ዳር መገናኛ መስመር ላይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ በየቀኑ ንጹሃን ዜጎች፣ ነጋዴዎችና ተማሪዎች ከሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ እየተመረጡ እንደሚታገቱ እየተገለጸ ነው።
አጋቾቹ ከእገታው በኋላ ለቤተሰቦች ስልክ በመደወል ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የሚጠይቁ ሲሆን፣ መክፈል የማይችሉ ዜጎች ላይ የሚደርሰው አካላዊ ስቃይና ግድያ አካባቢውን የፍርሃት ቀጠና አድርጎታል።
ከዜጎች እገታ ባሻገር፣ በዚሁ መስመር ላይ የሚንቀሳቀሱ የጭነት መኪናዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃትም ተባብሷል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በርካታ የጭነት መኪናዎች በታጣቂዎች ጥቃት እየደረሰባቸው ሲሆን፣ አንዳንዶቹም ሙሉ በሙሉ በእሳት እንዲጋዩ ተደርገዋል። ይህም በክልሉ የንግድ እንቅስቃሴና የሸቀጦች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል።
ከጎንደር ከተማ ጥቂት ኮሎሜትሮች ርቀት ላይ ዜጎች በጠራራ ፀሐይ ሲታገቱና ንብረት ሲቃጠል መታየቱ፣ የክልሉ የጸጥታ አካላት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ ማሳያ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፤ ይህ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸም አረመኔያዊ ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም እና በመንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተጓዦች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲከበር የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የሕዝብ ተወካዮች ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።
በአንጻሩ የክልሉ ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች ግን ክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈጹም ሰላም ነው የሚል ንግግር ሲያደርጉም ይስተዋላል፡፡












