Home / ማህበራዊ / በሕፃፅ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለከፋ ረሃብና ሞት ተዳርገዋል

በሕፃፅ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለከፋ ረሃብና ሞት ተዳርገዋል

በትግራይ ክልል ሕፃፅ ተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች በሰው ሰራሽ ረሃብ፣ በበሽታና በዱር አራዊት ጥቃት ለከፋ ሰብአዊ ቀውስ መጋለጣቸውን የዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ገልጸዋል።

ፓርቲዎቹ ፤ ከጦርነት የተረፉ ንጹሐን ዜጎች በአሁኑ ወቅት በረሃብ እየተሰቃዩ እንደሚገኙና ሕፃናት በመጠለያ ቦታዎች ሳይቀር በጅብ እስከመበላት ለደረሰ ከባድ ስቃይ ተጋልጠዋል ብለዋል።

የዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ገዥው ቡድን ከሕዝብ ደህንነት ይልቅ ለሥልጣኑና ለቡድናዊ ጥቅሙ ቅድሚያ በመስጠት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ሕዝቡን ለፖለቲካ ቁማር ታጋች አድርጎታል ሲል ወቅሷል። በሌላ በኩል ኢሕአፓ የደረሰውን ችግር “ትልቅ የሰብዓዊነት ልሽቀት” ሲል የገለጸው ሲሆን፣ ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ ማድረግ የዜግነት ግዴታ እንጂ እንደ እርዳታ ሊታይ አይገባም ብሏል።

ሁለቱም ድርጅቶች ይህ ዘግናኝ ሰብአዊ ቀውስ ከሚዲያ እይታ ተደብቆ እንዲቆይ መደረጉ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ገልጸው፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ረድኤት ድርጅቶች በአስቸኳይ አጣዳፊ እርዳታ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግና የትግራይ ሕዝብ ካለበት የሞትና የስቃይ አዙሪት እንዲወጣ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል።

በመጠለያው የሚገኙ ተፈናቃዮች ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ የሰብዓዊ እርዳታ ዕጦት እንደሚያጋጥማቸው እና ይህንንም ተከትሎ ለጋሾች አፋጣኝ እርዳታ እንዲያደርጉላቸው አበክረው ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *