Home / ማህበራዊ / በጋሞ ልማት ማህበር ስም የተገዛች ጀልባ በታጣቂዎች መታገቷ ተነገረ

በጋሞ ልማት ማህበር ስም የተገዛች ጀልባ በታጣቂዎች መታገቷ ተነገረ

የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃውን አስተባብሏል

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የጋሞ ልማት ማህበር ንብረት የሆነች አነስተኛ ጀልባ በታጣቂዎች ታግታ መወሰዷን ምንጮች ገለጹ። ምንጮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ እንደተናገሩት “ባይራ” የተሰኘችውና 30 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላት አነስተኛ ጀልባ፣ በአባያ ሀይቅ ላይ ጎብኚዎችን ይዛ በምትንቀሳቀስበት ወቅት ከአዞ እርባታ ጣቢያ በቅርብ ርቀት ባለች ደሴት አካባቢ ስትጓዝ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መውደቋ ተሰምቷል።

በወቅቱ በጀልባዋ ላይ የነበሩ ሰዎች በገንዘብ ድርድር መለቀቃቸው ቢገለጽም፣ ጀልባዋ ግን እስካሁን በአጋቾች ቁጥጥር ስር መሆኗን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰው መረጃ ያሳያል፡፡ እንደምንጮቹ ገለጻ ከሆነ፤ ድርጊቱን የፈጸሙት በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ መንግስት ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራቸው ታጣቂዎች ሳይሆኑ እንዳልቀረ ተናግረዋል። ጀልባዋ ከአዞ እርባታ ማዕከል ተነስታ እስከ ሞጬ ደሴት፣ ነጭ ሳር እና እስከ ዲላ ድረስ የቱሪስት መጓጓዣ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ የተገዛች እንደነበረችም ታውቋል።

የጋሞ ዞን አስተዳደር ጀልባዋን ለማስመለስ ከታጣቂዎቹ ጋር ድርድር መጀመሩን የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢወጡም፣ ጉዳዩ እስካሁን በምስጢር ተይዞ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የጋሞ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው ሲመልሱ “እየተወራ ያለው መረጃ ፍጹም ውሸት ነው” በማለት እገታው አለመፈጸሙን አስተባብለዋል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *