በትግራይ ክልል ባለፉት አራት ዓመታት ማለትም ከ2014 እስከ 2018 ሩብ ዓመት ድረስ በጾታዊ ጥቃት ብቻ የ22 ሴቶች ሕይወት ማለፉን ሆርን ፍሪኩዮንሲ ከክልሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሰምቷል።
ይህ መረጃ የሰሜኑ ጦርነት በሴቶችና ሕጻናት ላይ የጣለውን ከባድ ሰብዓዊ ቀውስና የስነልቦና ጠባሳ በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል። የክልሉ የሴቶችና ማህበራዊድ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዓለማት አማረ፣ ክልሉ የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑትን ጨምሮ ከ150 ሺህ በላይ ያህሉ ድጋፍ የሚፈልጉ ሴቶች አሉት ብለዋል። ይህ ቁጥር የተገኘው ከሰሜኑ ጦርነት መጀመር ወዲህ ባለው ጥናት ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ ከፍ ያለውን ድርሻ የሚይዘው የጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች መሆናቸውን ምክትል ኃላፊዋ አብራርተዋል። ሕይወታቸው ካጡ ሴቶች መካከል ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ራሳቸውን ያጠፉም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዓለማት አማረ የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ባለው ጊዜ በትንሹ 22 ሴቶች በጾታዊ ጥቃት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ 75 ያህል ሴቶችና ሕጻናትም የመደፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል ብለዋል። በክልሉ የነበረው ጦርነት ጾታዊ ጥቃትን እንደ መሳሪያ አድርጎ የሴቶችን አካላዊና ስነልቦናዊ ደኅንነት አደጋ ላይ የጣለበት አሳዛኝ እውነታ መሆኑ ተመላክቷል። አሁን ላይም በክልሉ ያሉ ሴቶችና ሕጻናት አስቸጋሪ ሁኔታን እያሳለፉ እንደሚገኙና ለዚህም ከፍተኛ የሆነ አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስረድተዋል። በተጨማሪም ከፕሪቶሪያው ውል መፈረም እና የጦር መሳሪያ ድምጽ መሰማት በክልሉ ውስጥ ቢቆምም ቤቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ግን አሁንም እንዳልቆመ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የጦርነቱ ቀጥተኛና ቀሪ ውጤቶች የሆኑት የአካል ጉዳት፣ የስነልቦና ቀውስ፣ የመፈናቀል እና የኑሮ መስተጓጎል ሴቶችና ሕጻናት ከሌላው የማኅበረሰብ ክፍል የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ተመላክቷል። በትግራይ ክልል ለሚገኙ የጥቃት ሰለባዎች ተገቢው የሕክምና፣ የስነልቦና፣ የሕግ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲደርስ የክልሉ ቢሮ ጥሪውን አቅርቧል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት የሕወሓት እና የጊዜያዊ መንግስቱ ከፍተኛ አመራሮች በጦርነቱ ወቅት ሕይወታቸውን ስላጡ ዜጎች እና የጾታዊ ጥቃት ስለደረሰባቸው ሴቶች በሚነገረው ቁጥር ዙሪያ የራሳቸውን አስተያየት ሲሰጡ እና ቁጥሩ አልተረጋገጠም እንዲሁም የተጋነነ ነው ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል፡፡










